በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ካርበን ክሬዲት ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ቀውስ ምላሽ ነው?


ይህ ፎቶ በኢትዮጵያ በድርቅ በተጠቃው የሶማሌ ክልል፣ አዳድሌ ወረዳ፣ ሂግሎ ቀበሌ አንዲት ሴት በጀሪካን የቀዳችውን ውሃ በአህያ ጭና ስትሄድ ያሳያል። Michael Tewelde/World Food Program/Handout via REUTERS.
ይህ ፎቶ በኢትዮጵያ በድርቅ በተጠቃው የሶማሌ ክልል፣ አዳድሌ ወረዳ፣ ሂግሎ ቀበሌ አንዲት ሴት በጀሪካን የቀዳችውን ውሃ በአህያ ጭና ስትሄድ ያሳያል። Michael Tewelde/World Food Program/Handout via REUTERS.

የዘንድሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ዋና አጀንዳ ከነበሩት ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ የአፍሪካ ሀገራት የካርበን ክሬዲት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው አዲስ እንቅስቃሴ ነው። ይሄ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚደርሱ እንደ ድርቅ፣ የጎርፍ አደጋ እና የምርት መጥፋት የመሳሰሉ ተጽእኖዎች ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ላሉ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ምን ማለት ነው?

(ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)

ካርበን ክሬዲት ለኢትዮጵያ የአየር ንብረት ቀውስ ምላሽ ነው?
please wait

No media source currently available

0:00 0:12:57 0:00

ለወትሮው ሚያዚያ እና ግንቦት ወሮች በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ለሚኖሩ አርሶ አደሮች የዘር ወቅት ነበር። ዘንድሮ ግን ዝናብ በወቅቱ ባለመጣሉ በአካባቢው በብዛት የሚመረተው በቆሎ እና ጤፍ የተዘራው በሰኔ መጨረሻ ነበር። ያም ሆኖ ግን እህል በሚሰበሰብበት ኅዳር ወር በድንገት የጣለው በረዶ የቀላቀለ ዝናብ በ2ሺህ 116 ሄክታር ላይ የተዘራ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ጓያ፣ ሽንብራ እና ሌሎች የጥራጥሬ እህሎችን ሙሉ በሙሉ አውድሟል። ከ93 ሺህ ኩንታል በላይ የሚጠጋ ምርትም ጠፍቷል። አቶ ሸጋው ነብሮ በቢቡኝ ወረዳ ሽማአቦ ቀበሌ ውስጥ ምርታቸው ከወደመባቸው አርሶ አደሮች አንዱ ናቸው።

በደቡብ ክልል አለ-ልዩ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አዳም አዲሱም እንዲሁ ለሶስት ተከታታይ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ በአካባቢው በስፋት ይምረቱ የነበሩ እንደ በቆሎ፣ ጤፍ እና ማሽላ የመሳሰሉ ምርቶች ምርት እንዳልሰጡ ይናገራሉ።

በዚሁ በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳ አካባቢ በግጭት ምክንያት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ላለፉት ሰባት አመታት በቀርሳ ቀበሌ በስደት የሚኖሩት አርሶ አደር ጴጥሮስ ቤንጆም የተለያዩ ሰዎችን ማሳ በማረስ ቢያንስ ቤተሰቦቻቸን ለመደገፍ ቢሞክሩም በዝናብ እጥረት እሳቸውም ሆነ የአካባቢው ማህበረሰብ ምርት ማግኘት እንዳልቻለ በምሬት ያስረዳሉ።

እነዚህ አርሶ አደሮች የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው የዝናብ እጥረት፣ ከፍተኛ የሙቀት መጨመር ወይም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና ጎርፍ ምክንያት ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ ናቸው።

ለአምስት ተከታታይ ወቅቶች ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ የኢትዮጵያን ደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎችን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ለአርባ አመታት ያልታየ ከፍተኛ ድርቅ ሚሊየኖችን የእርዳታ እጅ ጠባቂ አድርጓቸዋል። በምዕራብ አፍሪካም እንዲሁ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል።

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በግብፅ፣ ሻርም አል-ሼክ ሲካሄድ የቆየው 27ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የተካሄደውም በርካታ አፍሪካውያን የአየር ንብረት ቀውሶች ባስከተሏቸው የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ስቃይ ውስጥ ባሉበት ወቅት ነው። ጉባኤውን ከዚህ ቀደም ከነበሩት 26 ተመሳሳይ ጉባኤዎች ለየት የሚያደርገው ግን የአፍሪካ ሀገራትን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል አዲስ የካርበን ክሬዲት ወይም የካርበን ልቀት ድርሻ ሽያጭን የሚያበረታታ ፕሮጀክት እንዲቋቋም መደረጉ ነው። ይህ ካርበን ክሬዲት ፅንሰ ሀሳቡ ምንድነው? የስነ-ህዝብ ጤና እና አካባቢ ጥበቃ ኮንሶርቲየም የስምጥ ሸለቆ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አበባየሁ ካሳዬ ያብራራሉ።

አቶ አበባየሁ ካርበንዳዮክሳይድን ጨምሮ በካይ የተፈጥሮ ጋዞችን በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁት ያደጉ ሀገራት የሚገዙት ካርበን ክሬዲት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ሊደረጉ የሚገባቸውን የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ለማገዝ ይረዳል ይላሉ።

የአየር ንብረት ተፅእኖ ቀጥተኛ ክንዱን የሚያስርፍባቸው አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የአለም መንግስታት በየአመቱ ስለሚሰበቡበት ጉባኤም ሆነ የካርበን ክሬዲት ሀሳብ የሚያውቁት ምንም ነገር የለም።

ልክ እንደ አቶ አዳም አቶ ሸጋውም የግብርና ባለሙያዎች ከሰጧቸው መረጃ ውጪ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤውም ሆነ ካርበን ክሬዲት "የማውቀው ነገር የለኝም" ይላሉ።

ኬንያ፣ ማላዊ፣ ጋቦን፣ ናይጄሪያ እና ቶጎ የካርበን ገባያውን በፍጥነት ለመቀላቀል ቃል ከገቡ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። መንግስቶቻቸው እየተቀበሉት ያለውን የካርበን ልቀት ድርሻ ሽያጭ ያልተረዱት የችግሩ ገፈት ቀማሽ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ታዲያ የዚህ ሽያጭ ተጠቃሚ የሚሆኑት በምን መልኩ ነው የሚለውን አቶ አበባየሁ በምሳሌ ያስረዳሉ።

አንዳንድ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች እና የመብት ተሟጋቾች ግን ይህ የካርበን ገበያ በረጅም ግዜ እንዲመጣ የሚፈለገውን የከባቢ አየር ሙቀት ለመቀነስም ሆነ የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት አያስችልም በማለት ይቃወሙታል። ከእነዚህ አንዷ ኧርዝ ላይፍ አፍሪካ በተስኘ የደቡብ አፍሪካ ተቋም ውስጥ ዳይሬክተር የሆነቸው ማኮማ ላካላካላ አንዷ ናት።

"የካርበን ክሬዲት አሳሳቢው ነገር ካርቦንዳዮክሳይድን በብዛት ወደ ከባቢ አየር በመልቅቅ የሚበክሉት እና ዛሬ ላለንበት የአየር ንብረት መዛባት ተጠያቂ የሆንት አካላት መበከላቸውን እንዲቀጥሉ የሚያደርግ መሆኑ ነው። የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ይሄ ትክክለኛው መንገድ አይደለም። ምክንያቱም ምንም የሚጠቅመን ነገር የለውም። ይሄ ሌሎች አገሮች የሚለቁትን በካይ ጋዝ ወደራሳችን እንደመውሰድ እንደማለት ነው። ይሄ ደግሞ ምንም አይጠቅመንም።"

ይህን ስጋት በተወሰነ መልኩ አቶ አበባየሁም ይጋሩታል። በተለይ እ.አ.አ በ2050 የካርበንዳይኦክሳይድን እና ሌሎች በካይ ጋዞችን ልቀት ለማስወገድ የተቀመጠውን ግብ ለመምታት እንቅፋት እንደሚሆን ቢያምኑም ለጊዜው ያለውን አማርጭ መጠቀም ግን የተሻለ ነው ይላሉ።

በአየር ንብረት ጉባኤው ላይ የተሰበሰቡ የዓለም መሪዎች በየአመቱ 300 ሚሊየን የካርበን ክሬዲት በማውጣት የአፍሪካን የካርበን ገበያ ለማሳደግ እቅድ ይዘዋል። ይህም በአህጉሩ ከ30 ሚሊየን በላይ የስራ እድል እንደሚፈጥር ተመልክቷል። ነገር ግን አቶ ጴጥሮስ እና አቶ አዳሙን ጨምሮ በተከታታይ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ በድርቅ ለተጠቁ፣ ወይም እንደ አቶ ሸጋው ባልተጠበቀ ዝናብ የሰብል ምርታቸውን በጎርፍ በማጣቸው የሰው እጅ ጠባቂ ለሆኑ በሚሊየን የሚቆጠሩ የአፍሪካ አርሶአደሮች እና አርብቶ አደሮች ምን ያክል ለውጥ ያመጣ እንደሆነ ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

XS
SM
MD
LG