በዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ የሚገኘው የቨርጂኒያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እና የማህበረሰቡ አባላት ባላፈው እሁድ ምሽት በጅምላ አጥቂ የተገደሉትን ሶስት የትምህርት ቤቱ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ህልፈትን ለማሰብ ትናንት ሰኞ የሻማ ማብራት ስርዐት አከናውነዋል፡፡
የጅምላ ተኩስ ጥቃት በማድረስ ሶስት ተማሪዎችን ገድሏል የተባለው አጥቂ ትናንት ሰኞ እስከተያዘበት ድረስ የትምህርት ቤቱ ጊቢ ተዘግቶ እንዲቆይ የተደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ተማሪዎችና የትምህርት ቤቱ ሰራተኞች በሶስቱ ተማሪዎች ሞት የተሰማቸውን ሀዘን እንዲገልጹ ሁሉም ትምህርትና ተያያዥ እንቅስቃሴዎች ዛሬ ማክሰኞ እንዲቋረጡ መደረጉም ተመልክቷል፡፡
ፖሊስ የቀድሞ የእግር ኳሱ ቡድን አባል የነበረው የ22 ዓመቱ ክሪስቶፈር ዳንኤል በግድያው ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር መዋሉን ያስታወቀ ሲሆን የጥቃቱ ምክንያት እስካሁን አልታወቀም፡፡
ጥቃቱ የተፈጸመው ባላፈው እሁድ ምሽት ዋሽንግተን ይካሄድ የነበረውን ጨዋታ ተመልክተው ወደ ትምህር ቤታቸው ይመለሱ የነበሩ የአሜሪካ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋቾችን አሳፍሮ ከማቆሚያው ስፍራ በደረሰው አውቶብስ ላይ በተከፈተ የጅምላ ተኩስ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በጥቃቱ ሶስት ተማሪዎች ሲገደሉ በጽኑ ቆስሎ ሆስፒታል የሚገኘውን ጨምሮ ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸው ተመልክቷል፡፡