በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቀይ መስቀል ነፍስ አድን የህክምና እርዳታዎች ትግራይ ደርሰዋል


ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ

ጦርነቱ በድጋሚ ካገረሽበት ካላፈው ነሀሴ ወዲህ እና በፕሪቶሪያ እና ናይሮቢ የተደረጉ ስምምነቶች ከተፈረሙ በኋላ የመጀመሪያውን አስፈላጊ የህክምና አቅርቦት ቁሳቁሶችን የያዙ ሁለት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ዛሬ ማክሰኞ መቀሌ መግባታቸውን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ፡፡

ቀይ መስቀል መድሃኒቶችን የላከው በአፋጣኝ ወደ ሚፈለጉበት የህክምና ተቋማት መሆኑን በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ቡድን ኃላፊ ኒኮላስ ቮንአርክስ “ይህን ጭነት በመላካችን እጅግ በጣም ትልቅ እፎይታ ተሰምቶናል” ማለታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

ኃላፊው አክለውም “በክልሉ ያለው የጤና ሥርዓት በከባድ ጫና ውስጥ ይገኛል፤ እነዚህ መድሃኒቶች የህክምና እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች ህይወት አድን ናቸው።” ብለዋል፡፡

“ሁለት ዓመት በሞላው ግጭት ውስጥ እጅግ ከፍተኛ የሆነውን ስቃይ የተሸከሙ ሰዎች ባሉበት ሁኔታ፣ የሰብአዊ እርዳታው እንዲላክ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ በማድረግ ላይ የሚገኙ ወገኖችን እናመሰግናለን” ሲሉም የቀይ መስቀሉ ተወካይ መግለጻቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ፣ በክልሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አስቸኳይ ፍላጎት ለማሟላት፣ አርባ ቶኖች የሚሆኑ መሰረታዊ የህክምና እቃዎች፣ አስቸኳይ ጊዜ መድሃኒቶች እና የቀዶ ጥገና መሳሪዎች የጫኑ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በትግራይ የሚገኙ አንዳንድ የህክምና ተቋማት አገልግሎት የማይሰጡ ቢሆንም ክፍት የሆኑትም መሰረታዊ መድሃኒቶችን፣ መሳሪያዎችና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች የሚጎድሏቸው መሆኑን መግለጫው አመልክቷል፡፡

ተደራዳሪ ወገኖቹ በሚያደርጉት ጥረት እርዳታውን በመደበኝነት መስጠቱን እንደሚቀጥል ተስፋ ማድረጉንም የዓለም አቀፍ ቀይ መሰቀል ኮሚቴ መግለጫ አስታውቋል፡፡

XS
SM
MD
LG