በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ እና የሕወሓት ጦር አዛዦች ስምምነት ተፈራረሙ


የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የህወሃት ወታደራዊ ከፍተኛ አዛዦች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለማስፈጸም የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የህወሃት ወታደራዊ ከፍተኛ አዛዦች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለማስፈጸም የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የህወሃት ወታደራዊ ከፍተኛ አዛዦች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለማስፈጸም የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ። የናይሮቢው ስምምነት ምን ምን ነጥቦችን አካቷል?

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም የተደረሰውን ዘላቂ የግጭት ማቆም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ፣ ካለፈው ሰኞ ጥቅምት 28 ጀምሮ በኬንያ ናይሮቢ ሲወያዩ የቆዩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና የህወሃት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ዛሬ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል ፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እና የሕወሓት ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ስምምነቱን ለማስፈጸም የሚያስችል ፍኖተ ካርታ የሚያስቀምውን የስምምነት ሰነድ የተፈራረሙት ፣ ዛሬ ቅዳሜ ህዳር 3/2015 ዓ.ም ምሽት በናይሮቢ በተካሄደ ስነስርዓት ነው፡፡

ሁለቱ ወታደራዊ አዛዦች በተፈራረሙት የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሰነድ ላይ ከተካተቱ ነጥቦች መካከል፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀጽ 6 መሰረት የሚከናወነው የትጥቅ ማስፈታት ሂደት እንዴት እንደሚከናወን የሚዘረዝረው ነጥብ ይገኝበታል፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ ያጋራው እና በተራ ቁጥር 2 የተቀመጠው ይህ ነጥብ፣ በቅድሚያ ወታደራዊ አዛዦቹ በሚቀጥለው ማክሰኞ ህዳር 6/2015 ዓ.ም ወደ መደበኛ ቦታቸው ከተመለሱ በኋለ ባሉት 7 ቀናት ውስጥ ለሚመሩት የጦር ሰራዊት ገለጻ እንደሚያደርጉ ይገልጻል፡፡

በመቀጠል፣ በአራት ቀናት ውስጥ ታጣቂዎች ከግጭት ቦታዎች ለቀው ይወጣሉ።

ይህን ተከትሎ፣ የፌደራል ባለስልጣናት በሕገ መንግስቱ መሰረት በሁሉም አካባቢዎች ሃላፊነቱን ይረከባሉ።

ይህ ደግሞ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማስጀመርን እንደሚጨምር አመልክቷል።

የከባድ መሳሪያዎች ትጥቅን የማስፈታት ሂደት፣ የውጭ ኃይሎችን እና ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጭ የሆኑ ኃይሎችን ከክልሉ ከማስወጣት ሂደት ጋር ጎን ለጎን ይከናወናል ሲልም ሰነዱ ይደነግጋል፡፡

ከትጥቅ ማስፈታት ሂደት በተጨማሪ፣ በዘላቂነት ግጭት ማቆም፣ ሲቪሎችን መጠበቅ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ በናይሮቢው የስምምነት ሰነድ ላይ ከተካተቱ ነጥቦች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የሁለቱን አካላት ውይይት በዋና አሸማጋይነት ሲመሩ የቆዩት የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የፕሪቶያውን ስምምነት የማስፈጸም ተግባር “ወዲያውኑ የሚጀመር ይሆናል” ብለዋል፡፡ ይኸውም "ያልተገደበ ሰብአዊ አቅርቦትን፣ የመሰረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ፣ የሲቪሎችን ደህንነት መጠበቅ እና የህወሃት ታጣቂዎችን ትጥቅ መፍታትን የሚያካትት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ መሪዎች ለ5 ቀናት የተካሔደውን ውይይት በጥሩ መግባባት ማከናወናቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ ፣ የግጭት ማቆም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ በተዘጋጀው የፍኖተ ካርታ ሰነድ ላይ ተስማምተው መፈራረማቸው ከኢትዮጵያ ባሻገር ለአፍሪካ ቀንድም ሰላምና መረጋጋትን የሚያመጣ እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “ለህዝባችን ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቁርጠኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን” ካሉ በኋላ “የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በሙሉ ቁርጠኝነት እንሰራለን” በማለት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የትግራይ ክልል ህዝብ ችግር ላይ መሆኑን የተናገሩት የሕህወሃት ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው “የህዝባችን ስቃይ እስካሁን ቀጥሏል፤ ዛሬ ለስምምነቱ ቁርጠኝነታችንን የምናረጋግጠው የህዝባችን ስቃይ ያበቃል በሚል ተስፋ ነው” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

የሠላም ሂደቱን የሚመራው የአፍሪካ ሕብረት ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የህወሓት ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች በትግራይ እና አጎራባች ክልሎች እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያለምንም መከልከል ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ለማስቻል መስማማታቸውን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞችን ያልተገደበ እንቅስቃሴ ለማመቻቸት፣ ለሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች እና ድርጅቶች የደህንነት ዋስትና ለመስጠት እንዲሁም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ለሲቪሎች ጥበቃ ለማድረግም ተስማምተዋል ሲል በመግለጫው ጠቅሷል።

የሕብረቱ መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ ሁለቱ አካላት “አጠቃላይ የትጥቅ መፍታት፣ የብተና እና መልሶ ማቋቋም መርሃ-ግብር አፈፃፀም ላይ በዝርዝር የሚሰራ የጋራ ኮሚቴ ለማቋቋምም ተስማምተዋል”።

የፕሪቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 6 (ሠ) "የትጥቅ የማስፈታት ተግባራት ለከባድ መሳሪያዎች ቅድሚያ በመስጠት፣ የከፍተኛ አዛዦች ስብሰባ ካበቃ በሗላ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ አለበት" ይላል፡፡ ይሁን እንጂ "በከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ምክረሃሳብ መሰረት ጊዜው ሊራዘም ይችላል” ሲልም ይደነግጋል።

የኢትዮጵያ መንግስትም በናይሮቢ የተካሄደው የወታደራዊ አዛዦች ስብሰባ መጠናቀቁን ተከትሎ መግለጫ አውጥቷል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፣“በሰላም ስምምነቱ መሠረት የሕወሐት ታጣቂዎች ትጥቅ የሚፈቱበት ዝርዝር ዕቅድ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አዛዥና የሕወሐት ታጣቂዎች አዛዥ በናይሮቢ መክረው፣በተያዘው የጊዜ ገደብ ትጥቅ በሚፈታበትና መከላከያ ወደ መቀሌ በሚገባበት ዕቅድ ላይ ተስማምተዋል” ብሏል፡፡ “ዕቅዱም በቀጣይ ተግባራዊ ይደረጋል” ያለው መግለጫው፣ “በደቡብ አፍሪካ የተፈረመው የሰላም ስምምነት በተታቀደለት መንገድ እንዲሄድ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት እየሠራ ነው” ሲልም አመልክቷል።

ህወሃት ትላንት ባወጣው እና ዛሬ ምሽት በክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የፌስቡክ ገጽ በኩል ባጋራው መግለጫ፣ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት ገልጿል።

ነገር ግን በስምምነት ሰነዱ ላይ “የህወሃት ተዋጊዎች በሚል የተቀመጠው አገላለጽ ሊስተካከል ይገባል” ብሏል፡፡

“በተግባርም ህወሃት ሰራዊት የለውም” ሲልም አክሏል፡ “የትግራይ ሰራዊት ህዝቡን ከጥፋት ለመከላከል የተፈጠረ የምከታ ሰራዊት እንጂ የፖለቲካ ድርጅት ሰራዊት እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው፤ በመሆኑም በስምምነት ሰነዱ ህወሃትን ወክሎ የተላከ አካል ስለሌለ በህወሃት ስም የተደረገ የስምምነት ፊርማና የህወሃት ተዋጊ የሚል አገላለጽ ትክክለኛ እንዳልሆነ ታውቆ ማስተካከያ እንዲደረግ እታገላለሁ” ብሏል ሕወሓት በመግለጫው፡፡

XS
SM
MD
LG