የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ቀውስ በምድር ህልውና ላይ የተጋረጠ እንደሆነ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ላይ ተናገሩ። ሀገራቸው የአየር ንብረት ቀውስን ለማስቀረት ቃል በገባችው መሰረት ገንዘብ እያፈሰሰች መሆኑን ጠቁመዋል ።
በግብጽ ሻረም ኤል ሼክ የቀይ ባህር ሪዞርት ለተገኙት የዓለም መሪዎች እና ፖሊሲ አርቃቂዎች ባደረጉት ንግግር ባይደን የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቅረፍ ተግባራዊ ያደረገቻቸውን ጥረቶች እና ቁርጠኝነቶችን አረጋግጠዋል። ጥሩ የአየር ንብረት ፖሊሲ ፣ ጠንካራ መሰረት ላለው ፣ ችግር የሚቋቋም እና አካታች የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት እንደሚያስችል ለማሳየት ሀገራቸው ዋቢ እንደምትሆንም ጠቁመዋል ።
ባይደን ሀገራቸው እና አስተዳደራቸው በወሰዱት እርምጃ መሰረት የዝቅተኛ ካርበን ልቀት ግብን በ2030 እንደምታሳካ በሙሉ ልብ ለመናገር እንደሚችሉም ተናግረዋል ።
ዩናይትድ ስቴትስ የግሪን ሀውስ በካይ ጋዝ ልቀትን በትንሹ በ50 በመቶ ለመቀነስ በ2015 የፈረመው የፓሪስ ስምምነት ፈራሚ አካላት መካከል አንዷ ናት። የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገሪቱን ከዚህ ስምምነት በ2017 ዓም ቢያስወጧትም ፕሬዚደንት ባይደን ወደ ስልጣን ከመጡ በኃላ ይሄንን ውሳኔ ቀልብሰዋል ።