በኤርትራ የአራት ቀናት ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሀሙድ፣ ከኤርትራ የአየር ኃይል ጋር በመሆን ሥልጠና በመውሰድ ላይ የሚገኙትን የሶማሊያ ወታደሮች ጎበኝተዋል።
ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሀሙድ ትናንት ሐሙስ አሥመራ ሲገቡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አቀባበል አድርገውላቸዋል። መሪዎቹ ባካሄዱት ውይይት በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን ትብብር በተመለከተ ሃሳብ ተቀያይረዋል። በተጨማሪም በቀጠናው የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
ዛሬ፤ ዓርብ ደግሞ ፕሬዚዳንት ሐሰን እና የልዑካን ቡድናቸው የኤርትራን አየር ኃይል ጎብኝተዋል። በኤርትራ አየር ኃይል ኣዛዥ አስጎብኚነት የአየር ኃይሉን ሥራዎች የተመለክቱ ሲሆን፣ በዛ የሚሰለጥኑ የሶማሊያ ወታደሮችንም አግኝተው አነጋግረዋል። በሶማሊያ ወታደሮች የቀረበውን ወታደራዊ ሰልፍም ተመልክተዋል።
ፕሬዚዳንት ሐሰን የሚመሩትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብሺር ዑመር ጃምዕን ያካተተው የልዑካን ቡድን፣ የአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ትላንት ሐሙስ ነበር አሥመራ የገባው። ባለፈው ሐምሌ የመጀመርያ ጉብኝታቸውን ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሐሰን፣ በወቅቱ 7 ነጥቦችን የያዘ የመግባቢያ ሰነድ ከኤርትራ ጋር መፈራረማቸው ይታወሳል።
በዛን ወቅት ትኩረት ስቦ የነበረው ኤርትራ ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና ይወስዱ የነበሩት 5ሺህ የሶማሊያ ወታደሮች ጉዳይ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ "ወታደሮቹ በቅርቡ ወደ አገራቸው ይመለሳሉ" ብለው እንደነበርም ይታወሳል።
ይሁን እንጂ እስካሁን ይመለሱ፣ አይመለሱ የታወቀ ነገር የለም፡፡