በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ድርድር ለማድረግ በሯ ክፍት መሆኑን እንድታሳይ በግል መጠየቋን ዋሺንግተን ፖስት ዘገበ


የዩክሬን ወታደር 2022
የዩክሬን ወታደር 2022

የፕሬዘዳንት ባይደን አስተዳደር የሩሲያው ፕሬዘዳንት ብላድሚር ፑቲን ከስልጣን ካልተወገዱ በስተቀር ዩክሬን አሁን በሕዝብ ፊት የያዘችውን ማንኛውንም የሰላም ድርድር አልቀበልም የሚል አቋም በመቀየር ከሩሲያ ጋር ለመደራደር በሯን ክፍት መሆኑን እንድታሳይ እና ወደ ድርድር እንድትመጣ፤ በግል የዩክሬንን ባለስልጣናት እያበረታታ መሆኑን ዋሺንግተን ፖስት ትላንት ቅዳሜ መዘገቡን ሮይተርስ የዜና ተቋም ዘግቧል።

ጋዜጣው ስለውይይቱ የሚያውቁ እና ስማቸው ያልተገለጹ ሰዎችን ጠቅሶ፤ የአሜሪካ ባለስልጣናት ያቀረቡት ጥያቄ ዩክሬንን ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመግፋት ያለመ ሳይሆን፤ ጦርነቱ ለረዥም ዓመታት ሊቆይ እንደሚችል በመስጋት ድጋፋቸውን ለሩሲያ ሊሰጡ የሚችሉ ሃገራትን ሃሳብ ለማስለወጥ የተደረገ ስሌት መሆኑን ዘግቧል።

ጋዜጣው አነዚህ ውይይቶች የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ለስምንት ወራት በዘለቀው ግጭት ኪየቭን “እስከፈጀው ጊዜ ድረስ” ለመርዳት ከፍተኛ የሆነ እርዳታ ለመስጠት በአደባባይ ቃል በመግባታቸው እና በአለም ምጣኔ ሃብት ላይ ትልቅ ኪሳራ እና የኑውክሌር ጦርነት ስጋት በመደቀኑ መሃከል የባይደን አስተዳደር በጉዳዩ ላይ የገባበትን ውስብስብ ያሳያል ሲል ዘግቧል።

ጋዜጣው ፑቲን ድርድሩን በቁም ነገር እንደማይወስዱት የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣነት ከዩክሬን አቻቸው ጋር ተመሳሳይ የሆነ ግምገማ አላቸው ብሏል። ዘለንስኪ ከፑቲን ጋር ላለመነጋገር ያወጡት ገደብ ጦርነቱ በነዳጅ እና በምግብ ዋጋዎች ላይ ትልቅ ጫና ባስከተለባቸው በአውሮፓ፣ አፍሪካ፣ እና የላቲን አሜሪካ ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩንም አምነዋል።

አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን “የዩክሬን ስልቸታ የተሰኘው ነገር በአጋሮቻችን ላይ ያሳደረው ጫና እውነት ነው” ማለታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

የዋይት ሀውስ ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ዘገባው ትክክል ይሆን እንደሆነ ተጠይቆ ምላሽ አለመስጠቱን ዘገባው አክሎ አትቷል። ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ በበኩላቸው “ከዚህ በፊት ተናግረናል አሁንም እንደገና እንናገራለን ድርጊቶች ከቃላት በላይ ይናገራሉ” ያሉ ሲሆን “ሩሲያ ለድርድር ፍቃደኛ ከሆነች ሃይሏን ከዩክሬን ማስወጣት እና የቦምብ እና የሚሳይል ጥቃቶቿን ማቆም አለባት” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

XS
SM
MD
LG