በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፌዴራል መንግስትና የህወሃት ወታደራዊ አመራሮች ከነገወዲያ ሰኞ በኬንያ ናይሮቢ እንደሚገናኙ ተገለፀ


በስተግራ የኢትዮጵያ መንግስት ወኪል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ በስተቀኝ የህወሃት ወኪል ጌታቸው ረዳ የሰላም ስምምነቱን ሲፈርሙ
በስተግራ የኢትዮጵያ መንግስት ወኪል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ በስተቀኝ የህወሃት ወኪል ጌታቸው ረዳ የሰላም ስምምነቱን ሲፈርሙ

በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አዲስ አበባ ለሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት መናገራቸው ተዘግቧል።

በማብራሪያቸውም በስምምነቱ መሠረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት የሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች የስልክ ልውውጥ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

የሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች ሰኞ (ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም) በኬንያ ናይሮቢ እንደሚገናኙ እና ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት እንደሚጀምሩ አምባሳደር ሬድዋን ተናግረዋል።

የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላቱ በበኩላቸው፣ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መደሰታቸውን ገልጸው፣ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውም ተገልጿል።


የስምምነት ሰነዱ የህወሃት ታጣቂዎችን ትጥቅ አፈታት በተመለከተ፣ ስምምነቱ በተፈፀመ በ24 ሰዓታት ውስጥ በሁለቱ አካላት ከፍተኛ ወታደራዊ ኮማንደሮች መሀል ግንኙነት እንዲፈጠርና በሂደቱ ላይ በ5 ቀናት ውስጥ ውይይት እንዲያደርጉ ይደነግጋል።

ቀጥሎም በኮማንደሮቹ ስምምነት መሰረት፣ ከኮማንደሮቹ ስምምነት በኋላ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ ለከባድ መሳርያዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ የትጥቅ ማስፈታቱ ተግባር እንዲጀመር ተወስኗል፡፡ ትንንሽ መሳርያዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የትጥቅ አፈታት ሂደቱ፣ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ሁለቱ አካላት በደቡብ አፍሪካ በፈረሙት የስምምነት ሰነድ ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG