በጎዳና ላይ የተቃውሞ ሰልፍ የዛሬ ቅዳሜ የመጨረሻው ቀን እንደሚሆን የኢራን ሃያል አብዮታዊ ዘቦች አስጠነቀቁ። ይህም ይመንግስቱ የጸጥታ አካላት ሃገሪቱን እየናጣት ያለውን ተቃውሞ ለማስቆም ኃይል ለመጠቀም መወሰናቸውን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።
የ22 ዓመቷ ኩርዳዊት ማህሳ አሚኒ በስነምግባር አስከባሪ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ሳለች ህይወቷ ማለፉን ተከተሎ ኢራን በተቃውሞ እየተናወጠች ትገኛለች። ይህም እ.ኤ.አ ከ1979 አብዮት ወዲህ በሃይማኖታዊው መንግስት ላይ ከተደቀኑ ትላልቅ አደጋዎች መሃከል አንዱ ተደርጎ ታይቷል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ሁሴን ሳላሚ “ወደ ጎዳና ላይ እንዳትወጡ ዛሬ የግርግሩ የመጨረሻ ቀን ነው!” ሲሉ በጠንካራ ቃላት ያስጠነቀቁ ሲሆን እስላማዊው መንግስት ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ጠላቶቻችን ያሏቸውን የውጭ ሃገራት ለዓመጹ መቀጣጠል በመንስዔነት ይወቅሳሉ።
ሳላሚ “ይህ እኩይ ተግባር የተፈለፈለው በዋይት ሀውስ እና በጽዮናዊያን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ሴቶች ከፍ ያለ ሚና እየተጫወቱ ባለበት በዚህ ዓመጽ ኢራናዊያን ይህን መሰሉን ማስጠንቀቂያዎች ቸል ሲሉ ታይተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ደም መፋሰሱ ዛሬም መቀጠሉን ዘገባዎች አመላክተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ዱጃሪክ ትላንት ዐርብ በሰጡት አስተያየት የኢራን ባለስልጣናት “የሴቶችን መብትን ማክበርን ጨምሮ የህዝቡን ህጋዊ ቅሬታዎች እንዲፈቱ” ሲሉ አሳስበዋል።