በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ ቀውስ በዓለም እጅግ ከከፉት አንዱ ነው - ዋይት ሃውስ


የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን-ፒየር ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ 
የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን-ፒየር ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ 

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም “ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ዛሬ፤ ሰኞ ተጀምሯል” ያሉትን አፍሪካ ኅብረት-መር የሰላም ንግግር ላመቻቹትና ላስተናገደችውም ለደቡብ አፍሪካ የዩናይትድ ስቴትስን የአድናቆት መልዕክት የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን-ፒየር ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ አሳውቀዋል።

ለአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ ተጠሪ ኦባሳንጆ፣ እንዲሁም ለአፍሪካ ኅብረቱ ቡድን አባላት፤ የሃገሪቱ የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ፑምዚሌ ምላምቦ ምፆጋ፣ ለኬንያ ፕሬዚዳንት ኬንያታ ስምምነቱን እንዲያመቻቹ ‘ደቡብ አፍሪካ እየሰጠች ነው’ ላሉት ድጋፍም የመንግሥታቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን ባለፈው ወር ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ንግግር ሲያደርጉ ያስተላለፉትን መልዕክትም ዣን-ፒየር አስታውሰው “የኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆምና ለመላ ህዝቧም ደኅንነቱን ለመመለስ የሰላም ሂደት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ለዚህም ዩናይትድ ስቴትስ ጥልቅ ወደሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መግባቷንና የድርድሩን ክንዋኔም መደገፏን ገልፀው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኳ አምባሳደር ማይክ ሐመር ወደ አካባቢው ሄደው ለጥቂት ሣምንታት እዚያው መቆየታቸውን ጠቁመዋል። ልዑኩ በድርድሩ ላይ እንደሚሣተፉም አስታውቀዋል።

ወደ ሁለት ዓመታትን ካስቆጠረ ግጭት በኋላ “የኢትዮጵያው ሰብዓዊ ቀውስ በዓለም እጅግ ከከፉት አንዱ” መሆኑን ቃል አቀባይዋ ጠቁመው “ካለፈው ነኀሴ አንስቶ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በስፋት በመታገዱ፣ ምግብና የጤና አገልግሎት ግብዓቶች በብዙ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ እየተሟጠጡ በመሆናቸው ተጨማሪ እርዳታ አሁኑኑ ካልገባ የተራበው ህዝብ፣ በተለይ ህፃናት በአስደንጋጭ ቁጥር መሞት ይጀምራሉ” ብለዋል።

“ለዚህ ግጭት ወታደራዊ መፍትኄ የለም” ሲሉ በድጋሚ ያሳሰቡት ካሪን ዣን-ፒየር ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ የትግራይ ባለሥልጣናትም ወደ አፍሪካ ኅብረት-መሩ ንግግር ከልቦናቸው እንዲገቡ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ባልተገደበ ሁኔታ ለኢትዮጵያዊያኑ እንዲደርስ፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይቀጥሉና የኤርትራ ወታደሮችም ከሰሜን ኢትዮጵያ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

“ወገኖቹ ልዩነቶቻቸውን በውይይት እንዲፈቱና ተጨማሪ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲከላከሉ ዩናይትድ ስቴትስ ታሳስባለች” ብለዋል ዣን-ፒየር።

“የጭካኔ አድራጎቶችን የፈፀሙ በተጠያቂነት እንዲያዙም ለሚመለከታቸው ወገኖች በቅርብ ቀናት በግልፅ አሳውቀናል” ብለዋል የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን-ፒየር የዕለቱን መግለጫቸውን በከፈቱበት ኢትዮጵያን በሚመለከተው መልዕክታቸው።

XS
SM
MD
LG