"ፕሬዚዳንት ባይደን አገራቸው ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ፣ የጦር ወንጀል እና ሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን በሚያስከትል ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ለቆዩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ጊዜያዊ የስደት ከለላዎችን መስጠታቸው ፍጹም ትክክል ነው።” ሲሉ የህግ መወሰኛው ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር የኒውጀርሲው ዴሞክራት ሴናተር ባብ ሜኔንዴዝ ትናንት ባወጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡
ሜኔንዴዝ ይህን ያስታወቁት የባይደን አስተዳደር “ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከትናንት በስቲያ፣ ጥቅምት 10/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለ18 ወራት የሚቆይ ጊዜ ጊዜያዊ የከለላ ፍቃድ እንዲሰጣቸው” በሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በኩል መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ ነው፡፡
ሴናተር ሜኔንዴዝ በመግለጫቸው "በኢትዮጵያ ያለውን ግጭትና ተኩስ በአፋጣኝ ለማስቆም፣ እንዲሁም ግፍ የፈፀሙትን ተጠያቂ ለማድረግ ማዕቀብን ጨምሮ በእጃችን ያሉትን መሳሪያዎች ሁሉ መጠቀም አለብን፣ አሁን በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሰላም ወደ አገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ጥበቃቸውን ማጠናከር፣ የጠንካራ ፖሊሲ አካሄድ አስፈላጊ አካል ነው።” ብለዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የሃገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ትናንት ባወጣው መግለጫ “በግጭት፣ በሰብዓዊ ቀውስ፣ በምግብ እጥረት፣ በጎርፍ፣ በድርቅ እና በመፈናቀል ምክንያት ወደ ሃገራቸው መመለስ የማይችሉ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ያለው ሁኔታ እስከሚሻሻል በአሜሪካ እየሰሩ መቆየትና መሥራት ይችላሉ” ማለቱ ይታወሳል፡፡