የማላዊ ፖሊስ በሰሜን ማላዊ ምዚምባ ወረዳ በሚገኘ ደን ውስጥ በጅምላ ተቀብረው የተገኙ ኢትዮጵያዊያን ናቸው የተባሉ 25 ወንዶች የውጭ አገር ዜጎች አሟሟት እያጣራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ፖሊስ እንደገለጸው የመንደሩ ነዋሪዎች የጅምላ መቃብሩን ያገኙት በጫካው ውስጥ የዱር ነፍሳትን በማደን ላይ እያሉ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በሟቾቹ ላይ የተደረገው ቅድመ ምርመራ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን እንደሚያሳይ ተገልጿል፡፡
ፒተር ካላያ የማላዊ ፖሊስ አገልግሎት ቃል አቀባይ ይህንን ሲያስረዱ “የእነዚህን ሰዎች ስምና ዜግነት የሚያመለክቱ ሁለት ጊዜያዊ የጉዞ ሰነዶችን አግኘተናል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ የሚል የአገር ስም የተጻፈባቸው የስልክ ሲም ካርዶችን አግኝተናል፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ የምንይዛቸው ህገወጥ ፍልስተኞች አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን አስቀድመን ማወቃችን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ናቸው ከሚል መደምደሚያ እንድንደርስ መነሻ ሆኖናል፡፡ ብለዋል፡፡
ካላያ እንዳሉት አንድ ወር የሆነውን የጅምላ መቃብር ያገኙት በምታንጋታናጋ ደን ውስጥ የዱር ነፍሳትን ሲያድኑ የነበሩ የመንደሩ ሰዎች ናቸው፡፡
ለሰዎቹ ሞት ምክንያት ምን እንደሆን ለመመርመር የህክምና ባለሙያዎች የአስክሬን ምርመራ እያደረጉ መሆኑንም ካላያ ለቪኦኤ ተናግረዋል፡፡
የሟቾቹ አስክሬን እንደገና የሚቀበርበትን ስፍራ ለመወሰን ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም ቃል አቀባዩ አመልክተዋል፡፡ ቃል አቀባይ አክለውም፣
“አሁን በቅድሚያ መከተል ያለብን የአሰራር መርሆዎች ስላሉ ሁኔታዎችን እያቀናጀን ነው፡፡ እነዚህ የውጭ ዜጎች ስለሆኑ፡ እነዚያን መርሆዎች መከተል ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም አስክሬኖቹ በመፈራፈስ ላይ ናቸው፡፡ ለማንኛውም ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ማድረግ የምንችለውን እናያለን፡፡” ብለዋል፡፡
ፖሊስ ትናንት ሀሙስ በጫካው ውስጥ ሌላ የቀብር ቦታ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ በዚህ ቦታ አራት አስከሬኖች ተገኝተዋል፡፡ በዚህኛው መቃብር ውስጥ የተገኙት አስከሬኖች ዜግነታቸው አለመታወቁም ተገልጿል፡፡
ማላዊ ለውጭ ዜጎች በተለይም በማላዊ በኩል አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚጓጓዙ ኢትዮጵያዊያን የመሸጋገሪያ መስመር ነች፡፡
እነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ የማይታወቁ አቅጣጫዎችን ይጠቀማሉ፣ አንዳንድ ጊዜም ቀጣዩን ጉዟቸውን ሲያቅዱ ጫካው ውስጥ ይጠለላሉ፡፡
ለምሳሌ የባካሮንጋ ወረዳ ፖሊስ ትናንት በሰጠው መግለጫ ባላፈው ረቡዕ ያለምንም ምክንያት ጫካ ውስጥ ሲዘዋወሩ አገኘዋቸው ያላቸውን 72 ኢትዮጵያዊያንን አስሮ እየመረመረ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የፖሊስ ቃል አቀባይ ጆርጅ ሙሌዋ ኢትዮጵያዊያኑ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ማላዊ በመግባት ተከሰው የተያዙ ሲሆን በተባባሪነት ረድተዋቸዋል በተባሉ 10 የማላዊ ዜጎችም ላይ ክስ መመስረቱን ገልጸዋል፡፡
ሙሌዋ በመግለጫቸው “እስካሁንድረስ ምክንያቱን ማወቅ እንችላለን በሚል እነሱን የበለጠ በመመርመር ብዙ ነገር ለማግኘት ሞክረናል፣ ከአገራቸው ለምን እንደሚመጡ፣ ከቤታቸው መጥተው ለምን ጫካ ውስጥ እንደሚደበቁ፣ ይህ ለኛም ለማላዊ ዜጎችም ሆነ ለነሱም ስጋት ነው፣ ምክንያቱም ሰዎች በየቁጥቋጦ ውስጥ እየሞቱ መሆኑን እየሰማን ነው” ብለዋል፡፡
የማላዊ እና የኢትዮጵያ መንግሥታት ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ድጋፍ ጋር፣ በሕገ ወጥ መንገድ ገብተዋ በሚል የተያዙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እያደረጉ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የማላዊ ስድተኞች መምሪያ ቃል ቀባይ ፓስኳሊ ዙሉ “ሂደቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሌላ 22 የፍልሰተኞች ወደ አገራቸው መመለስ ችለናል፡፡” ካሉ በኋላ “በአጠቃላይ ከነሀሴ ጀምሮ 198 ዩሚሆኑትን ወደ አገራቸው መልሰናል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
የማላዊ መንግሥትን ጥፋተኛ የሚያደርጉ ተችዎች ችግሩ የሀገሪቱ ድንበር ክፍት በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ዙሉ በበኩላቸው ችግሩ ህገ ወጥ ስደተኞቹ የማላዊ ዜጎችን ድጋፍ ሰለሚያገኙ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ዙሉ አከለውም የማኅበረሰቡ አባላት በአካባቢያቸው የሚያጠራጥሩ እንቅስቃሴዎችን ወይም ጸጉረ ልውጥ ሰዎችን ሲያዩ ለጸጥታ ተቋማት ቢያስታውቁ የሚመጡት ፍልስተኞቹ ቁጥር ሊቀንስ ይችል ይሆናል ብለዋል፡፡