በሜድትሬንያን አካባቢ ያለው የነዳጅ ክምችት ምናልባትም የአውሮፓን የነዳጅ ፍላጎት ሊያሟላ ይችላል ሲሉ የግብጽ የሃይል ምኒስትር ተናግረዋል። ምኒስትሩ እንዳሉት ከአካባባው ጋዝን ለማውጣት በቂ መዋዕለ ነዋይ ከፈሰሰ፣ የአውሮፓን ፍላጎት ማሟላት ይቻላል።
ምኒስትሩ ይህን ያሉት “የምሥራቅ ሜዲትሬንያን የነዳጅ ፎረም” በተሰኘ ስብሰባ ላይ ሲሆን፣ የዓረቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በቆጵሮስ ለአንድ ቀን በተደረገው ስብሰባ ላይ በርካታ ሀገሮች እንደተገኙና፣ “በሜዲትሬንያን የሚገኘው የነዳጅ አቅርቦት፣ በተለይ በቀውስ ወቅት ለአውሮፓ ህይወት አድን ነው” ብለዋል።
ባለፉት ግዜያት ግብጽ የአውሮፓና የዓለም አቀፍ ገንዘብ ተቋማት በሜዲትሬንያን አካባቢ ለሚደረግ የነዳጅ ፍለጋ ገንዘብ ለመመደብ ያለመፈለጋቸውን ጉዳይ ስትወቅስ ቆይታለች። ውጥኑ ከውሃ ሥር ነዳጁን በማውጣት በቧንቧ ወደ አውሮፓ ለመላክ ያለመ ነበር ተብሏል።
የአካባቢው አጥኚዎች እንደሚሉት ግን፣ ጋዙን ማውጣት እንዲህ ቀላል አይሆንም፤ በቀጠናው ባሉ እኔ እበልጥ በሚሉ ተፎካካሪ ሃይሎችና፣ እንዲሁም በቱርክና በግብጽ እንዲሁም በግሪክና በቱርክ መካካል በአካባቢው ባለው የነዳጅ መሬቶች ይገባኛል ግጭት ምክንያት።