በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሳዑዲ አረብያ እና ዩናይትድ ስቴትስ በኦፔክ ውሳኔ ተወዛግበዋል


ፎቶ ፋይል፦ ከሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ በስተደቡብ የሚገኘው አል-ካርጅ አካባቢ የሚገኝ የአራምኮ የነዳጅ ዘይት ተቋም
ፎቶ ፋይል፦ ከሳዑዲ ዋና ከተማ ሪያድ በስተደቡብ የሚገኘው አል-ካርጅ አካባቢ የሚገኝ የአራምኮ የነዳጅ ዘይት ተቋም

ዩናይትድ ስቴትስ ተቃውሞዋን ብታሰማም የነዳጅ ዘይት አምራችና ላኪዎች ማኅበር (ኦፔክ) እና አጋር አገሮች፣ የነዳጅ ዘይት ምርት መጠኑን ለመቀነስ ባለፈው ሳምንት ባሳለፉት ውሳኔ ላይ የተሰነዘረው ትችት፣ “በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረተ አይደለም” ስትል ሳዑዲ አረቢያ ውድቅ አድርጋዋለች፡፡

ሳዑዲ አረቢያ በተጨማሪም ትናንት ዩናይትድ ስቴትስ ውሳኔው በአንድ ወር እንዲራዘም ያቀረበቸውን ጥያቄ በዐለም ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ መዘዝ ያስከትላል በማለት ውድቅ አድርጋዋለች፡፡

ዋይት ኃውስ በበኩሉ ውሳኔው የዐለም ኢኮኖሚውን ሊጎዳ እንደሚችል የሚያሳይ ትንታኔ ለሳዑዲ አረቢያ ማቅረቡን ገልጾ እና ኦፔክና አጋር አባል አገራት የነዳጅ ዘይት ምርታቸውን እንዲቀንሱ ድምጽ በመሰጠቱ ላይ ጫና አሳድራለች ሲል ሳዑዲ አረብያን ወንጅሏታል፡፡

የዋይት ኃውስ ቃል አቀባይ ጃን ከርቢ ባወጡት መግለጫ፣ “ገበያው ላይ የነዳጅ ዘይት ምርቱን ለመቀነስ የሚያበቃ ምንም መሰረት የለም፣ ነገሮች እንዴት እንደሚለወጡ እስከሚቀጥለው የኦፔክ ስብሰባ መጠበቅ ይቻል ነበር” ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ አያይዘውም “የኦፔክ አባል አገራት የሳዑዲን ውሳኔ እንዲደግፉ ግፊት የተደረገባቸው መሆኑ እንደተሰማቸው ለዩናይትድ ስቴትስ ተናግረዋል” ሲሉ ሳዑዲ አረብያ አሳድረዋለች ያሉትን ጫና ጠቅሰዋል፡፡

የነዳጅ አምራችና ላኪ አገሮች ያሳለፉትን ውሳኔ ተከትሎ ፕሬዚዳንት ባይደን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ፣ ውሳኔው በዩናይትድ ስቴትና በሳዑዲ አረብያ ግንኙነት ላይ “የሚያስከተለው መዘዝ ይኖረዋል” ሲሉመናገራቸው ይታወሳል፡፡

ሳዑዲ አረብያ ጉዳዩ ምንም ነገር የሌለበት የኢኮኖሚ ውሳኔ መሆኑን ብትገልጽም ዩናይትድ ስቴትስ ግን አልተቀበለችውም፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬንን በመወረሯ ምክንያት ምዕራባውያን የጣሉባትን የነዳጅ ዋጋ ገደብ ለምትቃወመው ለሞስኮ ተንበርክካለች ስትል ሳዑዲ አረብያን ትከሳታለች፡፡

በጉዳይ ዙሪያ በዩናይትድ ስቴትስ እና በሳዑዲ አረብያ መካከል የሚደረገው መመላለስ ለአስርት ዓመታት የኃይልና ደህንነት ትብብር በነበራቸው ሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረውን የቀዘቀዘ ግንኙነት ይበልጥ እንዲሻክር ሊያደርገው እንደሚችል ተሰግቷል፡፡

XS
SM
MD
LG