የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን የሥራ ጊዜን ለአንድ ዓመት አራዘመ።
መርማሪ ኮሚሽኑ በግጭት ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲቆይ የወሰነው በጠባብ የድምጽ ብልጫ ትናንት ዓርብ ባሳላፈው ውሳኔ መሰረት መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ (ኤኤፍፒ) ዘግቧል፡፡
የሥራ ጊዜው እንዲራዘም በአውሮፓ ህብረት የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ 21 ደጋፊዎችን ሲያገኝ 19 አገሮች ተቃውመውታል፡፡
ከሌሎች ስድስት አገሮች ጋር ድምጸ ተአቅቦ ካደረገቸው ማላዊ በስተቀር የምክር ቤቱ አባላት የሆኑት ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ተቃውመውታል፡፡
ባለሙያዎቹ መርማሪዎች ከጥቅምት 2013 ጀምሮ በግጭት ውስጥ ስለምትገኘው ኢትዮጵያ ሁኔታ በሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት 2023 መጀመሪያ ላይ ለኮሚሽኑ የቃል ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ተነግሯል፡፡
በጄኔቭ የኢትዮጵያ ተወካይ ድምጽ ከመሰጠቱ አስቀድሞ ባስተላለፉት የትዊት መልዕክት “ ኢትዮጵያ አልተቀበለችውም፤ የምክር ቤቱ አባላት፣ ይህን የፖለቲካ አካሄድ በመቃወም ድምጽ እንዲሰጡ ትጠይቃለች” በማለት አሳስበው ነበር፡፡
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች (ሂዩንማን ራይትስ ዎች) በበኩል የመርማሪዎቹ የሥራ ጊዜ መራዘሙ " ጥቃት የፈጸሙት ሁሉ አንድ ቀን ለፍርድ ሊቀርቡ እንደሚችሉ ለተፋላሚ ወገኖች ጠንካራ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው " ብሎታል፡፡
አምነስቲ ኢንተርሽናል ይህ ውሳኔ “በኢትዮጵያ በቀጠለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ተጎጂ ለሆኑ ወገኖች አንድ የሚደግፋቸው አካል መኖሩን ስለሚገልጽ ተስፋ ይሰጣል” ብሏል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ ውሳኔውን ትደግፋለች ያሉት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ “የኢትዮጵያ መንግሥት እና በዚህ ግጭት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች በሙሉ ሁሉን አቀፍና ግልጽ የሆነ የሽግግር ፍትህ ሂደትን ለመደገፍ ቃል መግባት አለባቸው፡፡ ከመጀመሪያውም ጀምሮ እንደተናገርነው የቀውሱ መፍትሄ ለድርጊቱ ኃላፊ የሆኑትንም ተጠያቂ ማድረግንም የሚጨምር ሲሆን እነዚያን ጥረቶችንም በመደገፍ በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡” ብለዋል፡፡