ኢንዶኔዥያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የእግር ኳስ ስቴዲዮም፣ በደጋፊዎች መካከል፣ ትናንት ቅዳሜ ምሽት በተቀሰቀሰ ሁከት በተፈጠረው መተረማመስና መረጋገጥ፣ 174 ሰዎች ሲገደሉ 180 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነገረ፡
በአደጋው ተጎጂዎች መከካል ሁለት ፖሊሶች የሚገኙበት ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች የሞቱ በተፈጠረው መረጋገጥ መሆኑን የስምራቅ ጃቫ ፖሊስ ኃላፊ ኒቾ አፊንታ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የኢንዶኔዥያ ፕሬሚየም ሊግ ጨዋታ ፐርሴባያ የተባለው ቡድን አሬማን 3 ለ 2 በማሸነፉ ያልተደሰቱ የአሬማ ደጋፊዎች ወደ ሜዳው ዘልቀው በመግባት የቡድኑን ተጫዋዎች ማሳደዳቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በፖሊሶችና በደጋፊዎች መካከል የተፈጠረውን ግብግብ የተመለከቱ ደጋፊዎች ከስቴዲዮሙ ፈጥነው ለማምለጥ በየመውጫዎቹ ትምርስምስና መጨናነቅ በመፈጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተረጋግጠው መሞታቸውን የፖሊስ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
የኢንዶኔዥያ ፕሬዚዳንት ጃኮ ዊዶዶ በቴሌቭዥን በሰጡት መግለጫ፣ በአደጋው ማዘናቸውን ገልጸው፣ የስፖርት ሚኒስትር፣ የፖሊሲ ኃላፊውና የኢንዶኔዥያ የእግር ኳስ ማህበር፣ የእግር ኳስ ግጥሚያዎችና የደህንነት አሰራራቸውን እንዲገመግሙ ጠይቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የጸጥታ ሁኔታዎች እስኪሻሻሉም ድረስ ለጊዜው ውድድሮች እንዳይካሄዱ ማዘዛቸውንም አስታውቀዋል፡፡