በላቀ ተሰጥኦ የበርካታ የሙዚቃ አፍቃሪያንን ልብ የገዛው ኢትዮጵያዊው ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ባደረበት ሕመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
ማዲንጎ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ዛሬ ለሕክምና መኪናውን ራሱ እያሽከረከረ ወደ ክሊኒክ ከሄደ በኋላ መሆኑን የሙያ አጋሮቹ ተናግረዋል።
የቀብር ሥነ ስርዓቱን የፊታችን ሐሙስ በአዲስ አበባው ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ለማካሄድ መታቀዱንም ለዚሁ የተቋቋመው ኮሚቴ ቃል አቀባይ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁ ሰይፉ ፋንታሁን ለአሜሪካ ድምፅ ገልጧል። ከዚያ ቀደም ብሎ የሽኝት ፕሮግራም የሚካሄድበት ቦታ እየተወሰነ መሆኑንም አመልክቷል።
በሌላ በኩል የድምፃዊውን ዜና እረፍት ተከትሎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት መልዕክት በማዲንጎ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚሁ መልዕክታቸው ማዲንጎን "ባጭር ዕድሜው ብዙ የሠራ" ሲሉ ገልጸውታል።
በማዲንጎ አፈወርቅ ሕይወትና ሥራዎች ላይ ያተኮረ ሰፋ ያለ ዘገባ ሰሞኑን ይዘን እንቀርባለን።