በጅቡቲ ወደብ መገንባት የሚያስችላቸውን መሬት የገዙት የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ወደቡን ያልተጣራ ነዳጅ ወደ ውጪ ለመላክ እና የተለያዩ እቃዎችን ለማስገባት እንደሚጠቀሙበት ገልፀዋል። ደቡብ ሱዳን በአሁኑ ወቅት ለውጪ ገበያ የምታቀርበውን ነዳጅ በሱዳን በኩል የምትልክ ሲሆን ኬንያ የሚገኘውን የሞምባሳ ወደብ ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ ለምታስገባቸው ምርቶች ትጠቀማለች።
የደቡብ ሱዳን የነዳጅ ሚኒስቴር ፓውት ካንግ ቾል ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቁት ሀገራቸው ወደብ አልባ እንደመሆኗ የውጪ ገበያውን ለመቀላቀል የሚቻለውን መንገድ ሁሉ ትጠቀማለች ብለዋል።
ዩጋንዳ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎም የወደብ እንቅስቃሴያቸውን ወደ ታንዛንያ ማዞራቸውን በቅርቡ ያስታወቁ ሲሆን ከአፍሪካ ታላላቅ ሐይቅ ሀገሮች መካከል የሞምባሳ ወደብን በብቸኝነት በመጠቀም ሩዋንዳ እና ብሩንዲ ብቻ ቀርተዋል።
ደቡብ ሱዳን 3.5 ቢሊዮን በርሜል የሚሆን የነዳጅ ክምችት እንዳላት የሚገመት ሲሆን ደቡብ ሱዳን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ፊታቸውን ከኬንያ ወደብ ማዞራቸው በምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ መካከል መከፋፈል እንዳይፈጥር ስጋት ፈጥሯል።
አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ኬንያ ከዳሬ ሰላም እና ጅቡቲ ወደቦች ጋር የገባችው ፉክክር ሀገሪቷን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚከታት እየገለፁ ነው።