በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አውሎ ነፋስ ፊዮና በፖርተ ሪኮ ጉዳት አደረሰች

"ፊዮና" ተብላ የተሰየመችው አውሎ ነፋስ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት የሆነችውን ፖርተ ሪኮን እና ዶሚኒካን ሪፖብሊክን ትናንት ከመታች በኋላ፣ ተርክስ እና ኬኮስ ወደ ተባሉት ደሴቶች ዛሬ አምርታለች።

በሰዓት 185 ኪሎ ሜትር ፍጥነት ያላት ፊዮና ከዝናብ ጋር ተቀላቅላ ፖርተ ሪኮንና ዶሚኒካን ሪፖብሊክን ስትመታ፤ መሰረተ ልማቶችን፣ የከተማ አገልግሎት ሰጪ ተቋሞችን እና መኖሪያ ቤቶችን አውድማለች።

በፖርተ ሪኮና ዶሚኒካን ሪፖብሊክ ዝናቡ እንደሚቀጥልና፣ ከ8 እስከ 10 ሴንቲሜትር ተጨማሪ ዝናብ እንደሚጥል የአየር ትንበያ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በፖርተ ሪኮ ቢያንስ ሁለት ሰዎች መሞታቸው ሲነገር በርካታ ነዋሪዎች ውሃ ተቋርጦባቸዋል።

የፖርተ ሪኮ ገዢ ፔድሮ ፒየርሉዊሲ በመሰረተ ልማትና መኖሪያዎች ላይ የደረሰው ጉዳት አስከፊ ነው ብለዋል።

የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ 900 የሚሆኑ ሰዎችን ከጎርፍ አደጋ ሲከላከል፤ የጭቃ ናዳም በብዙ ቦታዎች እንደተከሰተ ተነግሯል።

በዶሚኒካን ሪፖብሊክ የተከሰተው ማዕበል ደግሞ ወደቦችንና የውሃ ዳርቻ መዝናኛዎችን እንዲዘጉ አስገድዷል።

እንደ አየር ትንበያ ባለሙያዎች ከሆነ፣ ማዕበሉ ሐሙስ ወደ ቤርሙዳ ሲጠጋ ወደ ከፍተኛ አውሎ ነፋስ ሊያድግ ይችላል።


ተጨማሪ ይጫኑ

XS
SM
MD
LG