ካለፈው ሃምሌ ጀምሮ በማሊ ተይዘው የሚገኙ ወታደሮቿን በተመለከተ ቀጠናዊ ስብሰባ እንዲደረግ አይቮሪ ኮስት መጠየቋ “ማስፈራራት” እና “ማጭበርበር” ነው ስትል ማሊ ዛሬ መግለጫ አውጥታለች።
አይቮሪ ኮስት ወታደሮቼን አግታለች ስትል ማሊን ትከሳለች።
የቪኦኤዋ አኒ ራይዘንበር ከማሊ መዲና ባማኮ እንደዘገበችው በማሊ መንግሥት ቴሌቪዥን የተነበበው የመንግሥት መግለጫ፣ አይቮሪ ኮስት ጉዳዩን በተመለከተ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ስብሰባ ይጠራልኝ ማለቷ የማሊ መንግሥትን “በፍጹም አያሳሰበውም” ብሏል።
የአይቮሪ ኮስት ብሄራዊ የጸጥታ ም/ቤት ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ አይቮሪ ኮስት ወታደሮቼን አግታለች ብላ በመወንጀል፣ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቃለች።
ባለፈው ሐምሌ 49 የሚሆኑ የአይቮሪ ኮስት ወታደሮች የተባበሩት መንግሥታትን ሰላም አስከባሪ ኃይል ለመደገፍ ባማኮ አየር ማረፊያ ሲደርሱ፣ “ቅጥረኛ ወታደሮች” ናቸው በሚል ወንጅላ ማሊ በቁጥር ስር አውላቸዋለች።
በማሊ የቀድሞ የተመድ ልዑክ ቃለ አቀባይ የነበሩት ኦሊቨር ሳልጋዶ፣ የአይቮሪኮስት ወታደሮች መምጣትን በተመለከተ የተመድ ለማሊ አሳውቋል ብለው በትዊተር በመግለጻቸው ማሊ በአስቸኳይ ከሀገሯ አባራለች።
የአይቮሪኮስት ወታደሮች “ካለ ፈቃድና ትዕዛዝ፣ ማንነታቸውንም ሆነ የመጡበትን ጉዳይ ደብቀው፣ የጦር መሳሪያ በመያዝ የማሊን አፈር ረግጠዋል” ሲል የማሊ መንግሥት በትናንቱ መግለጫ ከሷል።
የማሊ ተቃዋሚ ፖለቲከኖች በአይቮሪኮስት የፖለቲካ ጥገኝነት እያገኙ ነው ሲሉ የማሊ ግዜያዊ ፕዚዳንት አሲሚ ጎይታ ባለፈው ሳምንት ከሰዋል።
ማሊ ምርጫዋን በማዘግየቷ ኤኮዋስ ባለፈው ጥር ማዕቀብ ከጣለባት በኋላ ከቀጠናው ማኅበር ጋር ፍጥጫ ውስጥ የቆየች ሲሆን ምርጫውን በሚቀጥለው ዓመት ለማድረግ ማቀዷን ተከትሎ ማዕቀቡ ተነስቷል።
ለማዕቀቡ ድጋፍ የሰጠችው ፈረንሳይ፣ ማሊ “ዋግነር ቡድን” በመባል ከሚታወቀው የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ጋር መስራቷ አሳስቦኛል በሚል ባለፈው ወር ጦሯን ከሀገሪቱ ጠራርጋ አስወጥታለች።