በሰሜናዊ የማሊ ክፍል በሚገኝ አንድ ከተማ ላይ ከእስላማዊ መንግስት ጋር ቁርኝት ያለው ጂሀዲስት ቡድን ባደረሰው ጥቃት በደርዘን የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት እና አንድ የታጣቂ ቡድን መሪ አስታውቀዋል።
በሳህል ቀጠና የሚንቀሳቀሰው እስላማዊ መንግስት ጋዎ ከተሰኘው ከተማ በ150 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ታላታዬ ከተማ ይህን ያህል መጠን ያለው ጥቃት ሲያደርስ የመጀመሪያው ነው።
ጂሃዲስቶቹ ማክሰኞ እለት ከአልቃኢዳ ጋር ቁርኝት ካለው 'እስላም ለሙስሊሞች ቡድን' ከተሰኘ ተቀናቃኛቸው እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ጋር ከፍተኛ ውጊያ አካሂደው እንደነበር ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ አካላት ተናግረዋል።
ውጊያው ለ3 ሰዓታት ከተካሄደ በኃላ ግን በሞተር ብስክሌት ድንገት ከተማዋን የወረሩት የእስላማዊው መንግስት ተዋጊዎች ከተማዋን መቆጣጠር ችለዋል።
በግጭቱ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር እስካሁን በውል ባይታወቅም፣ የአካባቢው ባለስልጣናት 45 ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን ሲያስታውቁ ሌላ ታጣቂ ቡድን ሟቾቹ 30 መሆናቸውን ተናግረዋል።