በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዋይት ሃውስ በኢትዮጵያ ጉዳይ


Mike Hammer
Mike Hammer

የፕሬዘዳንት ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ማይክ ሃመር በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ቀውስ ላይ ለመወያየት ወደ ኢትዮጵያ እየሄዱ መሆናቸውን የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን-ፒየር ትላንት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ተናግረዋል።

አምባሳደር ሃመር በጦርነቱ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ሁሉም አካላት ወታደራዊ አቁመው ወደ ሰላም ድርድር እንዲገቡ እንደሚያሳስቡ ቃል አቀባይዋ አመልክተዋል።

የኤርትራን ወደ ግጭቱ መመለስ፣ ከትግራይ ውጭ የቀጠለውን የህወሃት ጥቃት እንዲሁም የኢትዮጵያን መንግሥት የአየር ጥቃቶች ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታወግዝ ማይክ ሃመር እንደሚያሳውቁም ዣን-ፒየር ጠቁመዋል።

ለዚህ ግጭት ምንም ዓይነት ወታደራዊ መፍትኄ የለውም ብለዋል ቃል አቀባይዋ። አያይዘውም ከግጭቶቹ ማገርሸት በፊት በነበሩት ለአምስት ወራት የዘለቀ ሰብዓዊ ተኩስ ማቆም ዩናይትድ ስቴትስ ተስፋ ጥላ እንደነበር አመልክተው አሁን ግን ሰብዓዊ እርዳታ ለወታደራዊ ጉዳይ ሲባል እየተያዘ የመሆኑ ነገር ሃገራቸውን በጥልቅ እያሳሰበ መሆኑን ገልፀዋል።

ሁሉም ወገኖች እንዲታቀቡና ግጭት እንዲያበርዱ የጠየቁት ዣን-ፒየር የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንደገና እንዲጀመርና በተለይ መሠረታዊ አገልግሎቶች በብርቱ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ፈጥኖ እንዲደርስ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከንም በትዊተር ገፃቸው ላይ ተመሳሳይ መልዕክት ያዘለ ፅሁፍ አስፍረዋል።

በዋይት ሃውስና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን ማሳሰቢያዎች ላይ ከየትኛውም ወገን ፈጥኖ የወጣ ምላሽ እስካሁን የለም።

XS
SM
MD
LG