በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢራቁ የበቀል ጥቃት አራት ታጣቂዎች ተገደሉ


የሺኣ እስልምና መሪ የሙክታዳ አል ሳዳር
የሺኣ እስልምና መሪ የሙክታዳ አል ሳዳር

ኢራቅ ውስጥ በሺኣ ተቀናቃኝ ሚሊሻ ቡድኖች መካከል ትናንት ሀሙስ በተፈጸመ የበቀል ግጭት አራት ታጣቂዎች መገደላቸውን የኢራቅ ደህንነት ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡

ደቡባዊ ኢራቅ ውስጥ ባዝራ ከተማ ውስጥ የተፈጸመው ጥቃት የተከሰተው፣ አገሪቱን ወደ ወደ ጎዳና ላይ ጦርነት የከተታት የሰሞኑ የባግዳድ ግጭት ከተካሄደ ቀናት በኋላ መሆኑንም ተነግሯል፡፡

ከፍተኛ ተጽዕኖ ባላቸው የሺኣ እስልምና መሪ የሙክታዳ አል ሳዳርና በኢራን በሚደገፉት ተቃናቃኛቸው አሳይብ አኻል አል ሃቅ በሚመሩ ወታደራዊ ቡድኖች መካከል ትናንት ምሽቱን የተቀሰቀሰውን ግጭትና ሁከት ለመቆጣጠር የኢራቅ የጸጥታ ኃይሎች ወደ ባዝራ ከተማ መሰማራታቸው ተመልክቷል፡፡

ባግዳዳ ውስጥ የመንግሥት ዞን ተብሎ በከተለለው ክልል ውስጥ በአል ሳዳር ታማኞችና በኢራቅ ደህንነት ኃይሎች በተነሳ ግጭት 30 ሰዎች ሲሞቱ 400 የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸውን አሶሴይትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

ባላፈው ማክሰኞ አልሳዳር ተከታዮቻቸው አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በማዘዛቸው ግጭቱ መቆሙንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ግጭቶቹ በሙክታዳ አልሳዳር እና ካላፈው ዓመት የምክር ቤት አባላት ምርጫ በኋላ በኢራን በሚደገፉ ተቃናቃኝ ቡድኖቻቸው መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ውጤት መሆኑም ተመልክቷል፡፡

አልሳዳር ባላፈው ህዳር ምርጫ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የምክር ቤቱን መቀመጫ ቢያሸነፉም መንግሥት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ጥምረት መፍጥር አልቻሉም፡፡

በዚህ የተነሳም የሳቸው ድርጅት አባላት ከአገሪቱ ምክር ቤት ራሳቸውን ያገለሉ ሲሆን ደጋፊዎቻቸው በባግዳድ የሚገኘውን የምክር ቤቱን ህንጻ በመውረር አጥቅተዋል፡፡

አልሳዳር ምክር ቤቱ እንዲፈርስና ከሚቀጥለው ምርጫ በፊት ሌላ ምርጫ ከወዲሁ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱም ፓርቲዎች ፓርማላው በሚበተንበት መንገድ አልተስማሙም፡፡

የኢራቅ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የኢራቅ ምክር ቤትን መበትን ይቻል እንደሆነ ለመወሰን ለሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ቀጠሮ መያዙ ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG