በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቆቦ ከተማ ዙሪያ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች ጠቆሙ


የቆቦ ከተማ / ከጎግል ተቋም የተገኘ
የቆቦ ከተማ / ከጎግል ተቋም የተገኘ

እንደ አዲስ ያገረሸው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ቀጥሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት ባወጣው መግለጫ የሕዝብ ፍጅትን ለማስወገድ ሲል ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ መውጣቱን ገልጿል። በሌላ በኩል ዛሬ ምሽት ጀምሮ በቆቦ ከተማ ዙሪያ በኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎች እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ከተማዋ በአሁኑ ሰዓት ዳግም በኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ስር ስለመሆኗ በርግጠኝነት መጠቆም ያልቻሉ መረጃዎችም ወጥተዋል። የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው በቆቦ አቅራቢያ የሚገኙ ነዋሪዎች ማምሻውን በአካባቢው ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ እየተሰማ መሆኑን ገልፀዋል።ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከህወሓት በኩል የወጣ መረጃ የለም።

በሌላ በኩል ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የህወሓት ኃይሎች ቆቦ ከተማን መቆጣጠራቸውን ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ እናት ገልፀዋል። ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እኚሁ እናት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት ሚኒስትር በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ "ህወሓት ከፍተኛ ቁጥር ባለው የሰው ኃይል ቆቦ ከተማን ከብዙ አቅጣጫ እያጠቃ መሆኑን ገልፆ፣ በከተማ ውስጥ ሰርጎ ገቦችን በማስገባት የሕዝቡን ደህንነት አደጋ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ የከተማ ውስጥ ውጊያ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እየፈጠረ ነው" ብሏል፡፡

መግለጫው አክሎም የሕዝብን ፍጅት ለማስወገድ ሲባል የመከላከያ ኃይል የቆቦ ከተማን በመልቀቅና ወደ ኋላ መጥቶ ለመከላከል የሚያስችለውን ወታደራዊ ይዞታዎች ለመያዝ መገደዱን ጠቅሷል፡፡

በዚህም ምክኒያት ቆቦ ከኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ መሆኗን አስታውቆ ነበር።

የትግራይ ሰራዊት ወታደራዊ ኮማንድ የተባለው አካል ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ የአማራ ልዩ ኅይል ክፍለጦሮች፤የወሎ ፋኖ እና ሚሊሻዎች ከፌደራል መከላከያ ሀይል አካላት እግረኛ እዞች እና ሜካናይዝድ ክፍለጦሮች ጋር በመሆን ጦርነት እንደከፈቱበት ይፋ አድርጎ ነበር፡፡በአንጻሩ የፌደራሉ መንግሥት ህውሓትን በጦርነቱ ቀስቃሽነት ሲከስ ሰንብቷል፡

የአማራ፣ የአፋርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥታት አሸባሪ ሲሉ የገለጹት ኃይል ሰነዘረው ያሉትን ወታደራዊ ጥቃት አውግዘው መግለጫ አውጥተዋል። ህወሓት ርምጃዎቹ በትግራይ ሕዝብ ላይ ተከፍቷል ያለውን ጦርነት ለመቀልበስ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ሲናገር መቆየቱ አይዘነጋም።

/ተጨማሪ መረጃዎቹ እየተከታተልን እናቀርብላችኋላን/

XS
SM
MD
LG