በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“የትግራዩ ቀውስ ትኩረት ያላገኘው በ”ቆዳ ቀለም” ምክንያት ሊሆን ይችላል” ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም


ፎቶ ፋይል፦ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
ፎቶ ፋይል፦ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

በጦርነት በደቀቀችው ትግራይ ክልል “በሲቪሎች ላይ እየደረሰ ላለው እንግልት ዓለም ትኩረት ያልሰጠው ‘በዘረኛነት ምክንያት ነው’ የሚል ሃሳብ ያዘለ ንግግር የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አድርገዋል” ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።

“በዓለም እጅግ የከፋው ቀውስ” ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ በገለፁት ሁኔታ “መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዳያገኝ የተደረገው ስድስት ሚሊዮን ሰው ጉዳይ ስለምን የዩክሬንን ያህል ትኩረት አልተሰጠውም?” ሲሉ በስሜት መጠየቃቸውን የዜና ወኪሉ አክሎ አመልክቷል።

ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ዛሬ፤ ረቡዕ በኢንተርኔት መግለጫ የሰጡትና ትውልዳቸው ከትግራይ የሆነው ዶ/ር ቴድሮስ “ምናልባትም ምክያንቱ የሰዎቹ የቆዳ ቀለም ሊሆን ይችላል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ዶ/ር ቴድሮስ ባለፈው ሚያዝያ በሰጡት መግለጫ “የጥቁርና የነጭ ህይወት በአደጋ ጊዜ እኩል ትኩረት ይሰጠው እንደሆነም” መጠየቃቸውን ሮይተርስ አስታውሷል።

የጤና ድርጅቱ የአጣዳፊ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ማይክ ራያን በበኩላቸው በአፍሪካ ቀንድ ስለተከሰተው ድርቅና ረሃብ፣ ያንንም ተከትሎ ስለመጣው የጤና ቀውስ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን በተመለከተ ተችተዋል።

“በአፍሪካ ቀንድ እየሆነ ስላለው ነገር ማንም ግድ የሚሰጠው ያለ አይመስልም” ብለዋል ማይክ ራያን በዛሬው መግለጫ ላይ።

200 ሚሊዮን ሰዎች በሚኖሩበት የአፍሪካ ቀንድ ሚሊዮኖች እየተራቡ ሲሆን በምግብ እጦት ምክንያት የተከሰተውን የጤና ችግር ለመፍታት የ123.7 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግ የዓለም ጤና ድርጅት ጥሪ አድርጓል።

XS
SM
MD
LG