የአውሮፓ ኅብረት ሞዛምቢክ ውስጥ ለተሠማራው የደቡባዊ አፍሪካ ሀገሮች ወታደራዊ ተልዕኮ የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በአምስት እጥፍ ሊያሳድግ ማቀዱን አንድ የኅብረቱ የውስጥ ሰነድ አመለከተ።
ኅብረቱ ለአፍሪካዊው ወታደራዊ ተልዕኮ ድጋፉን ከፍ ለማድረግ ያቀደው አባል ሀገሮቹ በሩሲያ የነዳጅና የጋዝ አቅርቦት ላይ መተማመናቸውን ለመቀነስ ያስችላሉ ተብለው በታሰቡት የነዳጅ ፕሮጄክቶች ላይ እስላማዊ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት ሥጋት በደቀነበት ወቅት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት የነዳጅ እጥረት መፈጠሩ የአውሮፓ ሀገሮች ሰሜናዊው የሞዛምቢክ የባህር ጠረፍ ላይ ባለው የነዳጅ ክምችት ላይ ይበልጥ እንዲረባረቡ ያደረገ ሲሆን ምዕራባዊያን የተፈጥሮ ዘይት ኩባንያዎች ግዙፍ የቁፋሮና ብዝበዛ ጣቢያዎችን ለመገንባት ማቀዳቸው ተነግሯል።
ሩሲያና ቻይናም በደቡባዊ አፍሪካዊቱ ሀገር ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ ለመገዳደር ምዕራባዊያን እየሞከሩ መሆናቸው የሚሰማ ሲሆን የሩስያው የግል ወታደራዊ ኩባኒያ ቫግነር ከሦስት ዓመታት በፊት በፅንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች በተከታታይ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ ሞዛምቢክን ጥሎ መውጣቱ ይታወቃል።
ሞዛምቢክ የብዙ ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ፕሮጄክቶች በሚገኙበትና በነዳጅ ሃብት በከበረው ሰሚናዊው ካቦ ዴልጋዶ ክፍለ ግዛቷ ከዛሬ አምስት ዓመት ጀምሮ የእስልማዊ መንግሥት ቡድን ግብረ አበር ታጣቂዎችን ስትታገል ቆይታለች።
ከደቡባዊ አፍሪካ ሀገሮች የተውጣጣ ኃይልና የርዋንዳ የተናጠል ወታደሮች ባለፈው ዓመት ወደ ሞዛምቢክ ከዘመቱ ወዲህ ታጣቂዎቹ ጥቃታቸውን እንዳያስፋፉ ለመቆጣጠር መቻላቸው ቢነገርም የአካባቢው ሁኔታ አሁንም መረጋጋት የራቀው መሆኑ ተጠቁሟል።
የአውሮፓ ኅብረት ለደቡባዊ አፍሪካ ሀገሮቹ ወታደራዊ ሥምሪት የገንዘብ ድጋፉን ለማሳደግ ማቀዱን አንድ ቃል አቀባዩ አረጋግጠዋል።