በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጋምቤላ ውስጥ ስደተኞች ተገደሉ፤ ህፃናት ተጠለፉ


ጋምቤላ ውስጥ ስደተኞች ተገደሉ፤ ህፃናት ተጠለፉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:52 0:00

ጋምቤላ ውስጥ ስደተኞች ተገደሉ፤ ህፃናት ተጠለፉ

ጋምቤላ ክልል ውስጥ በሚገኘው አኩጉ መጠለያ ጣቢያ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ሁለት ስደተኞች መገደላቸውን፣ አንድ መቁሰሉንና ሁለት ህፃናት መጠለፋቸውን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

“ድንበር አቋርጠው ገብተው ጥቃቱን የፈፀሙት ከደቡብ ሱዳን የተነሱ የሙርሌ ጎሣ ታጣቂዎች ናቸው” ብለዋል የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኡቶው ኡኮት ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃል።

ከታጣቂዎቹ መካከል የተያዘ እንደሌለ የጠቆሙት አቶ ኡቶው የደቡብ ሱዳንና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሙርሌ ታጣቂዎችን ጥቃት በጋራ ለመከላከል ከዚህ በፊት ውይይት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ጋምቤላ ከሚገኘው የስደተኛችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስለጉዳዩና በአካባቢው ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በዚህ ዓመት በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ዘልቀው እየገቡ ሰው መግደላቸውንና ህፃናትን እያፈኑ መውሰዳቸውን፣ ከብት መዝረፋቸውን የገለፀው የጋምቤላ ክልል መንግሥት በስደተኞች መጠለያ ላይ ጥቃት ሲፈፀም ደግሞ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አስታውቋል።

ከትናንት በስተያ ሰኞ በተፈፀመው ጥቃት ላይ ከደቡብ ሱዳን ወገን የተሰማ ነገር የለም።

ባለፈው የካቲት ወደ ጁባ የተጓዘ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በሙርሌ ታጣቂዎች የሚፈፀመውን ጥቃት ጨምሮ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት ጋር መወያየቱ ተዘግቧል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

XS
SM
MD
LG