ማሊ ከሩሲያ የተበረከላትን በርካታ ጄቶችና ሂሊኮፕተሮችን መረከቧን የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥትና የሩሲያ መንግሥት መገናኛ ብዙሃን አስታወቁ፡፡
የሩሲያ መንግሥት ዜና ማሰራጫ ሪያ፣ ለማሊ ከተበረከቱ የጦር አውሮፕላኖች መካከል ሱኮይ 25 እና ኤል 39 ኦልባትሮስ የተባሉ ተዋጊ ጀቶች እንዲሁም አጥቂ ሂሊኮፕተሮች እንደሚገኙበት ዘግቧል፡፡
የማሊ መከላከያ ሚኒስትር ሳዲዮ ካማራ በማሊ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተላለፈ ንግግራቸው "ከዚህም የሚበልጡ ትልቅ ቁጥር ያላቸው የጦር አውሮፕላኖች" ተበርክተዋል ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
የጦር አውሮፕላኖቹን ባማባ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው የተቀበሉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሲሚ ጎይታ ሲሆኑ፣ በርክክቡ ስነስርዓት ላይ በማሊ የሩሲያ አምባሳደር ኢጎር ግሮሞይኮም መገኘታቸውን በፕሬዚዳንቱ ማህበራዊ መድረክ የወጡ ምስሎች አመልክተዋል፡፡
እ.አ.አ. ከ2012 ጀምሮ እስላማዊ መንግስት ተዋጊዎችን ለመዋጋት በሚደረገው ጦርነት ሩሲያ የማሊ የቅርብና አወዛጋቢ ወዳጅ መሆነዋ ተመልክቷል፡፡
በዚህ ዓመት ከእስላማዊ ተዋጊዎቹ ጋር የሚደረገው ጦርነት በአገሪቱ ማዕከላዊና ደቡባዊ ክፍል ተባብሶ መቀጠሉ ተነገሯል፡፡
ባላፈው ሰኔ 132 ሲቪሎች በእስላማዊ ታጣቂዎች ማዕከላዊ ማሊ ውስጥ መገደላቸው ሲገለጽ በደቡባዊ ማሊ ውስጥም በርካታ ጥቃቶች ተካሂደዋል፡፡
ባላፈው የካቲት፣ የፈረንሳይ መሪ ኢማኑኤል ማክሮን፣ በማሊ የሚገኙት የመጨረሻዎች የፈረንሳይ ወታደሮች ለቀው መውጣታቸውን ካሳታወቁ በኋላ፣ የሽብር ጥቃቱ ማየሉና የማሊ ወታደራዊ መንግሥት ከሩሲያ ቅጥረኞች ጋር አብረው መስራት መጀመራቸው ትልቅ ውጥረት ፈጥሮ መቆየቱ ተመልክቷል፡፡
የማሊ መንግሥት ግን ከሩሲያ ቅጠረኞች ጋር የማይሰራ መሆኑን በተከታታይ ሲያስተባብል ቆይቷል፡፡