የዩናይትድስቴትስ የጤና ባለሥልጣናት የዝንጀሮ ፈንጣጣን (መንኪፖክስ) ክትባት ለማዳረስ የወጣውን እቅድ አጽድቀዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የምግብና የመድሃኒት አስተዳደር ትናንት ባወጣው መግለጫ በአገሪቱ የተፈጠረውን የክትባቱን እጥረት በማየት ከዚህ በፊት ለእያንዳንዱ ሰው ይሰጥ ከነበረው ክትባት አሁን አንድ አምስተኛው እጅ ብቻ እንዲሰጥ ፈቃድ መስጠቱ ተመልክቷል፡፡
ትናንት የወጣው የጤና ባለሥልጣናቱ መግለጫ፣ በአነስተኛ መጠን ተቀንሶ የሚሰጠው ክትባት ከሙሉው ክትባት እኩል ውጤታማ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የዋይት ሀውስ ባለሥልጣናት አዲሱ ፖሊሲ አሁን ያለውን 444ሺ የክትባት መድሃኒት መጠን ወደ 2 ሚሊዮን ጥቃቅን የክትባት መድሃኒቶች እንደሚያበዛቸው ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ስለ ውጤታማነቱ በበቂ መረጃ ላይ የተደገፈ ጥናት ባለመደረጉ፣ የክትባቱን መጠን መቀነስ ተቃራኒ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ወደ 625ሺ ሙሉ የክትባት መድሃኒቶችን በየክፍለግዛቱ ማሰራጨታቸውንም ባለሥልጣናቱ አመልከተዋል፡፡