በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ እና ለመላው አፍሪካ ቀንድ ሰላም በቁርጠኝነት ትቆማለች


አምባሳደር ማይክ ሃመር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን
አምባሳደር ማይክ ሃመር፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

የአዲስ አበባው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ በዛሬው ዕለት ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እንዳደረገው፣ አምባሳደር ማይክ ሃመር የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ሰሞኑን የመጀመሪያቸው የሆነውን የኦፊሴል የሥራ ጉብኝታቸውን ባደረጉበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ እና በአጠቃላይም በክልሉ ሰላምን ለማጎልበት የሚያስችሉ ዕድሎች እና ጥረቶች ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ከአፍሪካ ህብረት ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል።

ልዩ መልዕክተኛ ሀመር እና በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን ከዲፕሎማቲክ ቡድን አባላት ጋር በመሆን በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተማ የመጀመሪያቸውን የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውንም መግለጫው ጨምሮ ገልጧል።

ልዩ መልዕክተኛው በአፍሪካ ሕብረት ሸምጋይነት በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ/ህወሓት/ መካከል ድርድር ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ አበረታተው፤ ሁሉም ወገን ከማናቸውም የኃይል ድርጊት እና ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጎት የሚንጸባረቅባቸው አፍራሽ እርምጃዎች እንዲቆጠብ፤ እንዲሁም ከጥላቻ ንግግሮች እንዲቆጠብ አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ጥረትና የተገኘውን ከፍተኛ መሻሻል በሥፍራው በመገኘት ያረጋገጡት የልዑካን ቡድኑ አባላት፤ የነዳጅ ወደ አካባቢዎቹ መላክ በመላው የአፋር፣ አማራ እና ትግራይ የዕርዳታ አቅርቦቱን በብቃት ለተቸገሩት ወገኖች ማዳረስ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2021ዓም የ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ወይም የ68 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ዕርዳታ ለመላው ኢትዮጵያውያን የጤና፣ የልማት እና የሰብዓዊ ፍላጎቶች ድጋፍ ማድረጓን የዘረዘረው ጋዜጣዊ መግለጫ በቅርቡም በኢትዮጵያ ለተከሰተው ድርቅ መርጃ የሚውል የ488 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደምትሰጥ የአዲስ አበባው የዩይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ይፋ ማድረጉን መግለጫው አስታውሷል።

“በዚህ ፈታኝ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዛ ለመስራት ቆርጣለች።” ብሏል።

አምባሳደር ሀመር የፖለቲካ ሰዎችን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን፣ ሴት መሪዎችን እና ምሁራንን ጨምሮ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ የተለያዩ ወገኖች ጋር መወያየታቸውንም መግለጫው አመልክቷል።

“የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆኜ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ክልሉ ባደረኩት ይፋ የሥራ ጉብኝት ዩናይትድ ስቴትስ የሃገሪቱን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በማይጻረር መንገድ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ያላትን ፍላጎት ገልጫለሁ።” ሲሉ አምባሳደር ሃመር የተናገሩትን የጠቀሰው መግለጫ፣ የአሜሪካ ህዝብ ባደረገው

ልግስና አገራቸው ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን የእርዳታ እጇን መዘርጋቷን ገልጧል።

“በምን ዓይነት ጥሩ መንገድ የጋራ ጥቅሞቻችንን እና ሰላምን ማራመድ እንችላለን በሚለው ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንድንወያይም ለተሰጠኝ ዕድል አድናቆቴን መግለጽ እፈልጋለሁ” ያሉት ልዩ መልዕክተኛ ሃመር ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማበልጸግ ስላሏት የልማት ዕቅዶቿም የተሻለ ተረድቻለሁ።” ብለዋል።

በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በሚከናወን ንቁ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ የናይል ወንዝ አቁርጦ በሚሄድባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ወገኖችን በሙሉ ተጠቃሚ ከሚያደርግ ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል.. ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።

አምባሳደር ጃኮብሰን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከታህሳስ 13 እስከ ታህሳስ 15/2022 ድረስ በሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ እና አፍሪቃ መሪዎች ጉባኤ ከዋይት ሃውስ የቀረበላቸውን ግብዣ አስታውሰዋል።

ዓለም አቀፍ ፈግዳሮቶችን ለመቅረፍ በጋራ እየሰራን ባለንበት ባሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መሪዎች በጉባኤው መሳተፍ የዩናይትድ ስቴትስን እና የኢትዮጵያን፣ እንዲሁም የዩናይትድ ስቴትስን የአፍሪቃን ግንኙነት ያጠናክራል።” ብሏል።

የልዩ መልዕክተኛ ሃመር ለሁለት ሳምንታት በሚጠጋ ቆይታቸው ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ረጅም የወዳጅነት ታሪክ እና እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የአፍሪካ ህብረት ለሚያደርገው ጥረት አገራቸው ያላትን ድጋፍ የሚያንፀባርቅ መሆኑን አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG