ዩናይትድስቴትስ በአፍሪካ ለሚገኙ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች የሚውል 127 ሚሊየን ዶላር መስጠቷን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ አስታወቁ።
ግሪንፊልድ ርዳታውን ይፋ ያደረጉት በጋና እያደረጉት ባሉት ጉብኝት ወቅት ሲሆን ገንዘቡ በተለይ በቡርኪናፋሶ፣ ቻድ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ማሊ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ኒጀር እና ሌሎች ሀገራት ውስጥ አዲስ በተፈጠሩና በተራዘሙ ግጭቶች ምክንያት ለተሰደዱ፣ ጥገኝነት ለጠየቁ እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መርጃ የሚውል ነው።
እርዳታው በመላው አፍሪካ የሚገኙ ከሰባት ሚሊየን በላይ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያዊዎችን እንዲሁም ከ25 ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ከመርዳታቱ በተጨማሪ በስደት ለረጅም ግዜ ለኖሩ እና ወደ ሀገራቸው መመለስ ለሚፈልጉ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚረዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በተለይ ስደተኞቹን ባስጠለሉ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እየጨመረ የመጣው የምግብ ቀውስ እና ዓለም አቀፍ እጥረት ጉዳት ላደረሰባቸው ህይወት አድን እና ኑሮዋቸውን ማስቀጠል የሚችል ርዳታ እንደሚሰጥ የገለፀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፣ ሌሎች ለጋሾች በአህጉሩ የሚታየውን ሰብዓዊ ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቋል።