ሊባኖስ የዛሬ ሁለት ዓመት 215 ሰዎችን የገደለውንና በቤሩት ወደብ ላይ የደረሰውን ፍንዳታ አስባ ስትውል፤ ነዋሪዎች በቅርቡ ለተናደው የወደቡ እህል ማከማቻ፣ በሙስናና ግዴለሽነት የሚጠረጥሯቸውን ፖለቲከኞች ተጠያቂ አድርገዋል።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ባለሙያዎች አሁን ከተናደው ጎተራ ውሰጥ እህሉን እንዲያወጣ መንግሥትን ሲወተውቱ ነበር።
ባለፈው ሰኔ ጎተራው በከፊል ሲናድ ሊባኖሳውያን አስከፊውንና የዛሬ ሁለት ዓመት የደረሰውን የወደብ ፍንዳታ በሃዘን እንዲያስታውሱ አድርጓል። የዛሬ ሁለት ዓመት ካለ አግባብ በወደቡ የተከማቸ አሞኒየም ናይትሬት የቤይሩትን ወደብ ሲያጋይ፣ ፍንዳታው በታሪክ ‘ኒኩሌር ያልሆነ ከባድ ፍንዳታ’ ተብሎ ተመዝግቧል።
በጎተራው የተከማቸው እህል በወደቡ ፍንዳታና፣ በከፍተኛው የበጋ ሙቀት ሲለበለብና ሲጨስ ለሳምንታት ከርሟል። የማኅበረሰብ አንቂዎች መንግሥት እሳቱን እንዲያጠፋና ጎተራውን በወደቡ ፍንዳታ ህይወታቸውን ላጡት መታሰቢያነት እንዲያውል ቢወተውቱም ሰሚ አላገኙም።
እንደ ወደቡ ፍንዳታ ሁሉ፣ ለጉተራው መደርመስ፣ ነዋሪዎች ‘የጥንቃቄ ደንቦችን የማያከብሩ’ ሲሉ የወነጀሏቸውን የፖለቲካና የደህንነት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
መንግሥት በበኩሉ ጎተራውን ለማፍረስ ሞክሮ ከፍንዳታው ሰለባ ቤተሰቦችና ከአደጋው ከተረፉ ሰዎች ‘ለምርመራው የሚያስፈልግ መረጃ ሊይዝ ይችላል’ በሚል ተቃውሞ ስለገጠመው ማፍረስ እንዳልቻለ ይናገራል።
ከወደቡ ፍንዳታ ሁለት ዓመታት በኋላ እንድም ግለሰብ በኃላፊነት እንዳልተጠየቀና የሰለባው ቤተሰቦች አሁንም ፍትህን ለማግኘት ትግል ላይ ናቸው ሲል የቪኦኤው ዴል ጋቭላክ ከአማን በላከው ዘገባ አመልክቷል።