በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ቀንድ ታይቶ ለማይታወቅ የምግብና የጤና ቀውስ ተጋልጧል


የአፍሪካ ቀንድ ታይቶ ለማይታወቅ የምግብና የጤና ቀውስ ተጋልጧል
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:11 0:00

የአፍሪካ ቀንድ ታይቶ ለማይታወቅ የምግብና የጤና ቀውስ ተጋልጧል

በአፍሪካ ቀንድ በከፍተኛ የምግብና የጤና ቀውስ ለተጋለጡ ሰዎች የሚውል የ 123.7 ሚሊዮን ዶላር አጣዳፊ እርዳታ በአስቸኳይ እንዲደረግለት የዓለም የጤና ድርጅት ተማጽኗል፡፡

በሶማልያ ኢትዮጵያና ኬንያ እስከ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች፣ ከወዲሁ እጅግ ለከፋው የረሀብ አደጋ መጋላጣቸውንና ከእነዚህ ከፊሎቹ ህጻናት መሆናቸውን ድርጅቶቹ አስታውቀዋል፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጉዳዮች ምላሽ ረዳት ዋና ዳይሬክተር ኢብራሂማ ሶሴ ፋል እንዳመለከቱት “አደገኛ” ያሉት የምግብ ደህንነት ዋስትና ችግር በቀጠናው የጤና ቀውስ እየፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የተመጣጠነ ምግብ እጥረቱ በከፍተኛ ሁኔታ የተባባሰ ሲሆን ኩፍኝና ኮሌራን ጨምሮ ወረሽኙም በዝቷል ብለዋል ረዳት ዳይሬክተሩ፡፡

ፋል ከሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር በስልክ በሰጡት መግለጫ ለከፍተኛው የረሀብ ቀውስ በሚሰጠው ምላሽ ውስጥ ጤና የሚጫወተው ድርሻ ብዙም አይታወቅም ብለዋል፡፡

“የጤና እንክብካቤ አነስተኛ የሚሆነው ሰዎች እጅግ በጣም በሚፈልጉበት ጊዜ ነው” ያሉት ፋል “ሰዎች ምግብ፣ ውሃና ለከብቶቻቸው ግጦሽ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ስለሚንቀሳቀሱ የሚያገኙት የጤና እንክባክቤ የተገደበ መሆኑ በጣም ያሳዝናል፡፡ ምናልባትም ደግሞ ምግብ በመግዛትና ወደ ሀኪም በመሄድ መካከል ያሉ ከባድ ምርጫዎችን ማድረግ ይኖርባቸውም ይሆናል፡፡” በማለት ተናግረዋል፡፡

“የዓለም ጤና ድርጅት ያቀረበው የብዙ ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጥሪ በጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማልያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ዩጋንዳ እንዲሁም በሌሎች በርካታ ሀገሮች ያሉ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ለመጠበቅና ለማጠንከር ይውላል” ሲሉም ፋል አስታውቀዋል፡፡

ረዳት ዳይሬክተሩ የእርዳታው ጥሪ ትኩረት በምግብ እጥረት ክፉኛ የተጎዱና የታመሙ ህጻናት የሚያስፈልጋቸውን የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

“የተፈናቀሉ ሰዎች ባሉባቸው አለመረጋጋት ሳቢያ የሚሰጠው የክትባት መጠን ቀንሷል፡፡ በኮቪድ ወረረሽኝ ወቅትም በእርግጥ የተቋረጠ የክትባት መርሃ ግብር አለ፡፡ ይህ በመሆኑም ለአደጋ የተጋለጡ ህጻናት የበዙ ሲሆን መሞትም ጀምረዋል፡፡ አሁን ራሱ የጤና ቀውስ ውስጥ ነን፡፡ የአመጋገብ ቀውስ ብቻ አይደለም...በርካታ ህጻናት በበሽታ እየሞቱ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ሁኔታው አስከፊ ሆኗል የግድ አንድ ነገር ማድረግ አለብን” ሲሉም ስለጤና ቀውስና የህጻናት ሞት ግንኙነት ተናግረዋል።

ፋል አክለውም “የዩክሬን ጦርነት ከተከሰተ ካላፈው የካቲት ወር ወዲህ የእርዳታ ድጋፎችን ለማግኘት የታየው ፉክክር እጅግ እየተባባሰ መጥቶ ለጥሪቶች መናመን ምክንያት ሆኗል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

“ይሁን እንጂ በዩክሬን ያለውን ቀውስ ብቻ በመደገፍ በአፍሪካ ቀንድ ሰዎች በረሀብና በበሽታ እንዳይሞቱ ለመከላከል ምንም አለማድረግ ህሊና የሚፈቅደው ነገር አይደለም” ሲሉ የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጉዳዮች ምላሽ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ኢብራሂማ ሶሴ ፎል ለዓለም አቀፍ ለጋሾች መልዕክት አስተላልፈዋል ፡፡

/ዘገባውን በድምጽ ለመከታተል የተያያዘውን ፋይል ይጫኑ/

XS
SM
MD
LG