በዓለም ላይ ተፅእኖ ለማሳደር በሚደረገው ፉክክር የሩሲያ እና የቻይናን ተሰሚነት ለመገዳደር የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንከን በመጪው ሳምንት ወደ ምስራቅ እስያ እና አፍሪካ ይጓዛሉ።
ብሊንከን ጉዞአቸውን ማክሰኞ እለት ወደ ካምቦዲያ በማድረግ የሚጀምሩ ሲሆን በቀጣይ ወደ ፍሊፒንስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ያጓዛሉ።
የመጀመሪያ መዳረሻቸው በሆነችው ካምቦዲያ በደቡብ ምስራቅ እስያ ቀጠና ፀጥታ ጉዳይ ላይ የሚካሄድ ጉባኤ ላይ የሚገኙ ሲሆን የሩሲያ እና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በስብሰባው ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ብሊንከን ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌይ ላቭሮቭ ወይም ከቻይናው አቻቸው ዋንግ ዪ ጋር በቀጥታ ይገናኙ እንደሆን ለምክትላቸው የምስራቅ እስያ እና የፓሲፊክ ጉዳዮች ሚኒስቴር ዳንኤል ክራይተንብሪክ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ በአሁኑ ወቅት የታቀደ መደበኛ ስብሰባ አለመኖሩን ተናግረዋል። ሆኖም ብሊንከን እና ዋንግ መደበኝ ያልሆነ የጎንዮሽ ንግግር ሊያደርጉ ይችላሉ የሚለውን ሀሳብ ውድቅ አላደረጉም።
ብሊንከን ወደ አፍሪካ የሚያደርጉት ጉዞ ሩሲያ በአህጉሩ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያደረገችውን ጥረት ተከትሎ የአሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል የሚደረግ ሲሆን የሚጎበኟቸው ደቡብ አፍሪካ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ በአህጉሩ እና በዓለም ደረጃ ትልቅ ሚና ያላቸው መሆናቸውን የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሞሊ ፊ አብራርተዋል።