በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ባይዶዋ ውስጥ ባለሥልጣን ከነልጃቸው ተገደሉ


ባይዶዋ
ባይዶዋ

የሶማሊያዋ ደቡብ ምዕራባዊ ከተማ ባይዶዋ ውስጥ ዛሬ በተጣለ የቦምብ ፍንዳታ አደጋ ሁለት ሰዎች መገደላቸውና ሌሎች ስምንት ሰዎች መቁሰላቸው ተገለፀ።

የተገደሉት የጥቃቱ ዒላማ የሆኑት የክልሉ የፍትህ ሚኒስትር ሼክ ሃሰን ኢብራሂምና ወንድ ልጃቸው መሆናቸውን እማኞችና የፀጥታ ባለሥልጣናት ገልፀዋል።

በጥቃቱ የሚኒስትሩን ሌላ ልጅ ጨምሮ ቢያንስ ስምንት ሰዎች እንደቆሰሉ ታውቋል።

ቦምቡ የፈነዳው ሚኒስትሩና ልጆቻቸው ከጁምዐ ፀሎት በኋላ ከመስጂድ እየወጡ ሳሉ እንደነበረ የደኅንነት ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ለዛሬው የቦምብ ጥቃት ኃላፊነት የወሰደ ባይኖርም ባለሥልጣናቱ ግን እንዲህ ያሉ ጥቃቶችን በማድረስ ተጠያቂ የሚያደርጉት የአልሸባብ ታጣቂዎችን ነው።

ቡድኑ ባለፈው ሣምንት ጥቃቱን በማባባስ በደቡብ ምዕራባዊ ሶማሊያ ባለሥልጣናትንና ሰላማዊ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከሁለት ቀናት በፊትም ክልሉ ውስጥ በሚገኙ ሁለት ከተሞች ውስጥ በደረሱ የቦምብ ፍንዳታዎች ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸውና ከሃያ የሚበልጡ ሌሎች ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG