የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያቋቋመው የሰብዓዊ መብቶች ባለሞያዎችን ያካተተ ዓለም አቀፍ ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተፈፀሙ የመብቶች ጥሰቶችን ለመመዝገብ ጥሪ አቀረበ።
ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና ተቋማት ከጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ግጭት ውስጥ የተካፈሉ ሁሉም አካሏት የፈፀሟቸውን የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ፣ ሰብዓዊነት እና የስደተኛ መብቶች ጥሰቶችን የሚያስረዱ ማንኛውንም መረጃ ለኮሚሽኑ እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርጓል።
https://www.ohchr.org/en/hr-bodies/hrc/ichre-ethiopa/call-for-submissions
መረጃዎቹ በተለይ ፆታን መሰረት አድርገው የተፈፀሙ ጥቃቶች እና የመብቶች ጥሰቶችን እንዲሁም የጥቃት አድራሾችን ማንነት ሊያጠቃልል እንደሚችልም አስታውቋል።
መረጃ አቅራቢዎች ከመብት ጥሰት በተጨማሪ የሽግግር ፍትህ፣ ተጠያቂነት፣ እርቅ እና ፈውስ ለማምጣት የሚያስችሉ የሚሏቸውን የመፍትሔ ሐሳቦችን የያዙ ሰነዶችን ኮሚሽኑ የጠየቀ ሲሆን መረጃዎቹ በእንግሊዘኛ፣ በአማርኛ እና በትግርኛ ቋንቋዎች መቅረብ እንደሚችሉ አመልክቷል።
መረጃ አቅራቢዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ድህረ ገፅ ላይ የተቀመጠውን ቅፅ በመሙላት ማስገባት የሚችሉ ሲሆን መረጃዎቹ እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ተጠናቀው መግባት እንዳለባቸውም አሳስቧል።