በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤም.ኤስ.ኤፍ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቅሬታ አሰማ


Ms Paula Gil, President of MSF Spain
Ms Paula Gil, President of MSF Spain

ኢትዮጵያ ለስድስት ቀናት ቆይተው የተመለሱት የድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን የስፓኝ ፕሮግራም ፕሬዚዳንት ፓውላ ጊል ባለፈው ዓመት ሰኔ አጋማሽ ላይ ትግራይ ውስጥ የተገደሉ ሁለት ኢትዮጵያዊያንና አንዲት ስፓኛዊት ባልደረቦቻቸውን ለመዘከርና የቡድናቸውን የውስጥ ግምገማ ሂደት ለሟቾቹ ቤተሰቦች ለማሳወቅ ወደ ክልሉ ለመሄድ ቢጠይቁም ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ፍቃድ አለማግኘታቸውን የቡድኑ የኢትዮጵያ ቢሮ አስታውቋል።

ጊል በሰጡትና ቡድኑ ለአሜሪካ ድምፅ በላከው መግለጫ “በዚህ ሣምንት መጨረሻ የአዲስ አበባ ጉብኝቴን ሳጠናቅቅ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ስሜት ነው የተሰማኝ” ማለታቸውን ጠቅሷል።

ፕሬዘዳንቷ አክለውም የሦስቱ ባልደረቦቻቸውን ግድያ ምርመራን በተመለከተ ባለሥልጣናቱን ለማነጋገር ለውጭ ጉዳይ፣ ለፍትሕና ለመከላከያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ጥያቄ ቢያቀርቡም ማንንም ማግኘት አለመቻላቸውን አመልክተዋል።

የጉዟቸው ዓላማ የማሪያ ፈርናንዴዝ ማቲስ ፣ የቴድሮስ ገብረማርያምንና የዮሃንስ ሃለፎም ረዳን ግድያ ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀ ምርመራ ውጤት ለመረዳትና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሆን ቁርጥ ያለ እርምጃ ለመውሰድና በሂደቱ ውስጥ ለመሳተፍ እንደነበር ገልፀዋል።

ፓውላ ጊል አያይዘውም ተቋማቸው “የሚችላቸውን መንገዶች ሁሉ በመጠቀም በባልደረቦቹ ላይ ለደረሰው ግድያ ተጠያቂነትን ለማምጣት ጥረቱን ይቀጥላል” ብለዋል።

ከሃያ ወራት ግጭት በኋላ ‘እየበረታ ነው’ ካሉት የምግብ እጥረት ጋር ተዳምሮ ሰዎች የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ ያሉበት ሁኔታ እንደሚያሳስባቸውም የስፓኝ ኤምኤስኤፍ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል።

ድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን /ኤምኤስኤፍ/ በሦስቱ ባልደረቦቹ ላይ የተፈፀመውን ግድያ በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ መቆየቱ ይታወሳል።

በመግለጫው ላይ የተጠቀሱትን መሥሪያ ቤቶች ለማነጋገር ቪኦኤ እየጣረ ይገኛል።

XS
SM
MD
LG