በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የመንግሥታቱ ድርጅት መርማሪዎች ኢትዮጵያ ናቸው


ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ
ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ

በድጋሚ የታደሰ

ትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ጦርነት ወቅት ‘ተፈፅመዋል’ የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲመረምር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተሰየመው ኮሚሽን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጉብኝቱን ትናንት፤ ሰኞ ጀምሯል።

ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች፥ የሰብዕናና የስደተኞች ደኅንነት ዓለምአቀፍ ድንጋጌዎች ጥሰቶችን እንዲመረምር ባለፈው ዓመት ታኅሣስ ውስጥ ሲቋቋም ሊታደስ የሚችል የአንድ ዓመት የአንድ ዓመት የሥራ ዘመን ተሰጥቶት እንደነበር ይታወሳል።

ኢትዮጵያ የኮሚሽኑም መቋቋም ‘ፍሬቢስ’ ነው ስትል እንደማትተባበር ገልፃ በወቅቱ ውድቅ አድርጋው የቆየች ቢሆንም በቅርቡ ግን እንዲገባ ፈቃድ ሰጥታለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት ትናንት ባወጣው መግለጫ “ከኮሚሽኑ ጋር የመተባበርን ጉዳይ እንደገና የምናጤነው በተግባሩና የመንግሥታችንን አቋም ማክበር አለማክበሩን ተመልክተን ይሆናል” ብሏል።

የኮሚሽኑ አባላት ትናንት ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን ለመንግሥቱ ቅርበት ያለውን ፋና ብሮድካስቲንግ ጠቅሶ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

የኬንያ፣ የሽሪ ላንካና የዩናይትድ ስቴትስ ባለሙያዎችን ያካተተው ይህ ኮሚሽን እስከ ፊታችን ቅዳሜ፤ ሐምሌ 23/2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚቆይና ሪፖርት እንደሚያወጣ ታውቋል።

ከኮሚሽኑ ጋር እንደሚተባበሩ አሳውቀው የነበሩት ትግራይን እያስተዳደሩ ያሉት ባለሥልጣናት ፌደራል መንግሥቱ በኮሚሽኑ ላይ “የራሱን ሃሳብ ለመጫንና ተዓማኒነቱን ለመሸርሸር ይጥራል” ብለው ከስሰዋል።

በጥቅምት 2013 ዓ.ም. በመንግሥቱ ኃይሎችና በህወሓት መካከል የተቀጣጠለው ጦርነት በቀጠሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የኤርትራን ጦርም ጨምሮ መላ ትግራይን አድርሶ ለአጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልሎችም የተረፈ ሲሆን በውጊያዎቹ ውስጥ በሲቪሎች ላይ ለተፈፀሙ የበረቱ ጥቃቶችና በደሎች ሁለቱም ወገኖች ሲወነጃጀሉ ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው መጋቢት የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ ወዲህ የተጋጋለ ውጊያ በአመዛኙ ጋብ ቢልም ክልሉ ግን በከበባ ውስጥ በመሆኑ የባንክ፣ የስልክ፣ የኢንተርኔት አገልግሎቶችና የነዳጅ አቅርቦት የበረታ ችግር መኖሩ እየተነገረ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ባካሄዱትና በዚህ ዓመት መጀመሪያ አካባቢ ባወጡት ሪፖርት በሁሉም ወገኖች በሰብዕና ላይ የተፈፀሙ ጥፋቶች መኖራቸውን የሚያመላክቱ ማስረጃዎችን ማግኘታቸውን ገልፀው ነበር።

XS
SM
MD
LG