ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣኖችን እጅግ የሚያስፋፋ የሆነው አዲሱ የቱኒዥያ ህገ መንግሥት ትናንት ሰኞ የተካሄደውን ውሳኔ ህዝብ በቀላሉ ማለፉን ድምፅ ሰጥተው በሚወጡ ሰዎች አስተያየት ላይ የተመረኮዘ ግምገማ ያሳያል። በውሳኔ ህዝቡ ድምፃቸውን የሰጡት ሰዎች ቁጥር ግን እጅግ ዝቅተኛ እንደነበር ተመልክቷል።
ባለፈው ዓመት ፕሬዚዳንት ካይስ ሳኢድ ሀገሪቱን "ለዓመታት ተሽመድምዳ ከቆየችበት ሁናቴ መታደግ አለብኝ" ብለው ፓርላማውን አግደው ራሳቸው በአዋጅ አስተዳደሩን ሲመሩ ቆይተዋል። ከዚያም ባለፈው ወር አዲስ ህገ መንግሥት አውጥተዋል።
አዲስ ህገ መንግሥት የአስተዳደሩን እና የፍትህ አካሉን ሥልጣን ለፕሬዚዳንቱ የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ የምክር ቤቱን ሥልጣን በማዳከም የፕሬዚዳንቱን ሥልጣን የሚቆጣተር አካል እንዳይኖር የሚያደርግ ነው።
የትናንቱ ህገ መንግሥታዊ ውሳኔ ህዝብ ይፋ ውጤት በአንክሮ እየተጠበቀ ሲሆን የምርጫ ኮሚሽኑ የድምፅ ውጤቱን ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚያሳውቅ እየተጠበቀ ነው።
የምርጫ ኮሚሽኑን የቦርድ አባላት ፕሬዚዳንቱ የቀየሩ ሲሆን ተቃዋሚዎች ውሳኔ ህዝቡ በዚህ ኮሚሽን በተካሄደ ድምፅ አሰጣጥ ተዓማኒነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ከቀደሙት ምርጫዎች ጋር ሲነጻጸር የነጻ ታዛቢዎች ቁጥር አናሳ መሆኑንም ተቃዋሚዎች አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንቱ ትናንት ድምፃቸው ሲሰጡ ውሳኔ ህዝቡን "የአዲስ ሪፐብሊክ መሰረት" ብለውታል።