የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በግብፅ፣ ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ እና ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ጉዞ ዛሬ መጀመራቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
ሐመር አንድ ሳምንት በሚቆየው በዚህ ጉዞአቸው ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጉዳዮች፣ የሁሉንም አካላት ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ ዲፕሎማቲክ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል እና ቀጠናው ሰላማዊ እና የበለፀገ እንዲሆን ያላትን ድጋፍ የሚገልፁ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
አዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ልዩ መልዕክተኛው የህዳሴ ግድብ ውይይቶች ከሚካሄድበት የአፍሪካ ህብረት ጋር ምክክር የሚያደርጉ ሲሆን በሰብዓዊ ርዳታ አሰጣጥ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ጥቃቶች ተጠያዊነት እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግስት እና በትግራይ ባለስልጣናት መካከል ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረትም ይመለክታሉ።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ፀጥታ እና ብልፅግና እንዲሰፍን ዩናይትድስቴትስ ሁሉን አሳታፊ ለሆነ የፖለቲካ ሂደት ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ መስጠቷን እንደምትቀጥልም መግለጫው ጨምሮ አመልክቷል።