በቅርቡ ከስልጣናቸው የለቀቁትን የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት የሚወዳደሩት ሁለቱ ተፎካካሪዎች ህገወጥ ስደትን ማስቆም ቀዳሚው ስራቸው መሆኑን እና መንግስት ስድተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያዘጋጀውን ፖሊሲ ሁለቱም እንደሚደግፉት አስታውቀዋል።
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለመሆን ከፍተኛ ፉክክር እያደረጉ የሚገኙት የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስቴር የነበሩት ሩሺ ሱናክ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሊዝ ትሩስ በግብር አከፋፈል እና የኢኮኖሚ እድገትን በማስቀጠል ጉዳይ ላይ ቢቃረኑም ህገወጥ ስደተኞችን አስመልክቶ ዛሬ ለጋዜጠኞች በላኩት መግለጫ ወደ ሩዋንዳ ለመላክ የውጣውን ፖሊሲ እንደሚደግፉት አመልክተዋል።
ትሩስ በመግለጫቸው "ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆንኩ የሩዋንዳ ፖሊሲ ሙሉ ለሙሉ ተፈፃሚ መሆኑን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ከሌሎች ሀገሮች ጋር በተመሳሳይ መልኩ የምንሰራበትን መንገድ እፈልጋለሁ" ብለዋል።
ሱናክም በተመሳሳይ ህገወጥ ስደት ከፍተኛ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ መሆኑን አስምረው "አንድ ሀገር ህገወጥ ስደተኞችን መልሶ ለመቀበል የማይተባበር ከሆነ በእርዳታም፣ በንግድም ሆነ በቪዛ ስለሚኖረን ግንኙነት ሁለተኛ ቆም ብዬም አላስብም" ብለዋል።