በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊላንድ ቢቢሲን አገደች


ሶማሊላንድ ቢቢሲን አገደች
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:46 0:00

ሶማሊላንድ ቢቢሲን አገደች

ከሶማሊያ ተገንጥላ ራሷን ሉአላዊ ሃገር አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊላንድ የእንግሊዝን የማሰራጪያ ጣቢያ ቢቢሲን አግዳለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሞቃዲሹ ፖሊስ ሁለት ጋዜጠኞችን ደብድቦ ማሰሩን አንድ የሶማሊያ የፕሬስ ነጻነት ቡድን አውግዟል።

ከየትኛውም ሀገር እውቅና ያላገኘችው ነገር ግን ራሷን እንደ ሉአላዊ ሀገር አድርጋ የምትቆጥረው የሶማሊላንድ ባለስልጣናት፣ የእንግሊዙ ዜና ማሰራጫ ጣቢያ ቢቢሲ፣ “በክብራችን እና በማንነታችን ላይ መጥቷል” እያሉ ነው።

የሶማሊላንድ የማስታወቂያ ምኒስትር ሳሌባን ዩሱፍ ኩር ትናንት ማክሰኞ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ የእንግሊዙ ዜና ማሰራጫ ጣቢያ የሀገራቸውን ክብርና ማንነት ዝቅ አድርጎ አዋርዷል ብለዋል።

የሶማሊላንድ መዲና በሆነችው ሃርጌሳ ላይ ሆነው ምኒስትሩ በሰጡት መግለጫ፣ ባለስልጣናት ረጅም ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ቢቢሲ ገለልተኝነቱን ስላጣና ከሶማሊላንድ ነጻነት በተቃራኒ ስለቆመ፣ እንዲታገድ ወስነዋል።

እገዳውም ወዲያውኑ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረዋል። “ሶማሊላንድ ዲሞክራሲያዊ ሀገር መሆኗን እንዲሁም ላለፉት 31 ዓመታት በሁለት እግሯ የቆመች ፣ ምርጫ በማድረግ አምስት ፕሬዝዳንቶችን የቀያየረች፣ እንዲሁም ሶስት የፓርላማ ምርጫ ያደረገች ሀገር መሆኗን ቢቢሲ እውቅና አይሰጥም። በተጨማሪም ቢቢሲ የሶማሊላንድ ህዝብ መስማት የማይፈልጋቸውን ቃላት ይጠቀማል።” ብለዋል።

ሶማሊላንድ በእንግሊዝ ስር ትደዳር የነበረች የሰሜን ሶማሊያ አካል የነበረች ስትሆን እ.አ.አ በ1991 ሶማሊያ በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ ነጻነቷን አውጃለች። ነገር ግን ሶማሊያም ሆነ የትኛውም ሀገር እውቅና አይሰጣትም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሶማሊያ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ኩባንያዎች በዕለት ተዕለት ስራቸው ላይ ችግር እየገጠማቸው ነው።

የሞቃዲሹ ቴሌቪዥንና ራዲዮ ጣቢያ በሆነው አርላዲ ሚዲያ ላይ የሚሰሩ አንድ ጋዜጠኛና ሌላ የካሜራ ባለሙያ ባለፈው ሰኞ በጸጥታ ሃይሎች ተይዘው ነበር ሲሉ የጣቢያው ሃላፊ አህመድ አሊ ኑር ለቪኦኤ ተናግረዋል።

“ጋዜጠናችንና የፎቶግራፍ ባለሙያችን ጥቃት ደርሶባቸዋል፣ ሽጉጥ ተተኩሶባቸዋል። ተደብድበው ታስረዋል። ስራቸውን በመስራት ላይ ሳሉ መሳሪያዎቻቸው ተነጥቆ የተወሰኑት ተሰባብረዋል። ከትናንት ጀምሮ ጉዳዩን በሚመለከት መረጃ አላገኘንም። ፍትህን እንጠይቃለን።” ብለዋል ኑር።

አብሽር ሞሃመድ ኑር ፋርሳ ጥቃት ከደረሰባቸው ጋዜጠኞች አንዱ ሲሆን ፤ “ሞቃዲሹ በቅርቡ በጣለው ዝናብ ምክንያት የወደሙ መንገዶችን በተመለከተ ዘገባ በመሥራት ላይ ሳሉ የጸጥታ አባላት መጥተው እንደደበደቧቸው ተናግሯል። “ለምን ያን እንደሚያደርጉንኳ አልነገሩንም። ከደበደቡን በኋላ የፎቶግራፍ ባለሞያውን ፖሊስ ጣቢያ ወስደው መሳሪያውን ሰባበሩት።” ብሏል።

የሶማሊያ ፖሊስ ቃል አቀባይ የሆኑት አብዲፋታህ ኣዳን ሃሳን ለቪኦኤ እንደተናገሩት ፖሊስ ወዲያውኑ እርምጃ በመውሰድ ጋዜጠኞቹ ላይ ጥቃት የፈጸመውን ወታደር በቁጥጥር ስር ሲያውሉ፣ ሌላው ባልደረባው ተሰውሮ ፍለጋ ላይ ናቸው።

“ግለሰቦች የጸጥታ አካላትን መለዮ ለብሰው ሕዝቡ ላይ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ። በዋዳጂር አውራጃ ጥቃት የተፈጸመባቸው ጋዜጠኞችን ችግር እጋራለሁ።” ያሉት አዳን “ ከክስተቱ በኋላ ከአርላዲ ሚዲያ እና ከፖሊስ ኮሚሽነሩ ጋር ተነጋግሬያለሁ። በመጨረሻም ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ዘብጥያ እንዲወርድ ተደርጓል።” ብለዋል።

ሶማሊያ ለጋዜጠኞች በዓለም እጅግ አደገኛ ቦታ ተደርጋ ስትቆጠር ባለፉት 12 ዓመታት 50 የሚሆኑ የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ተገድለውባታል። በጋዜጠኞች መብት ላይ የሚሰራው ሪፖርተርስ ዊአዝውት ቦርደርስ ሶማሊያን በአፍሪካ ለጋዜጠኞች እጅግ አደገኛ ቦታ ሲል ይግልጻታል።

XS
SM
MD
LG