ትግራይ ውስጥ በህወሓት ታጣቂዎችና በፌዴራሉ መንግሥት ጦር መካከል በተካሄደው ጦርነት የወደሙ የመሥረተ ልማት መዋቅሮችን መልሶ በመገንባት ሥራ የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም የሆነው የፕሮጀክት አገልግሎቶች ቢሮ ኃላፊነት ወስዶ እንዲያግዝ መንግሥት ዛሬ ስምምነት መፈራረሙን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ሌላው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋም የሆነው የዓለም ባንክ ለእነዚሁ መዋቅሮች ግንባታ ይውላል ያለውን የሦስት መቶ ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ባለፈው ሚያዝያ ለኢትዮጵያ መንግሥት በልገሳ መስጠቱ ተዘግቧል።
ይህንን የሦስተኛ ወገን የተባለና ብሄራዊ የማገገሚያ መርኃግብር አካል የሆን ፕሮጀክት አፈፃፀም ስምምነት በኢትዮጵያ ስም የፈረሙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴና በመንግሥታቱ ድርጅቱ የፕሮጀክት አገልግሎቶች ቢሮ በኩል ተወካይዋ ወርቅነሽ መኮንን መሆናቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ዘግቧል።
ፕሮጀክቱ በተጨማሪም በግጭቶች ለተጎዱ ማኅበረሰቦች ማገገሚያ እንዲሆን የታሰበ፤ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መልሶ በመገንባትና በማሻሻል የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን የሚቋቋም ኅብረተሰብን የመገንባት ዓላማም ያካተተ መሆኑ ተነግሯል።
ፆታ ላይ ላነጣጠረ ጥቃትና ሁከት ተጋላጮችን ማቋቋምንም ዋና ዓላማው ያደረገ ፕሮጀክት መሆኑም ታውቋል።