በመጨረሻው ዙር አጓጊ የነበረው የ2014 ዓ.ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት ተጠናቋል።
ዛሬ ሰኔ 24/2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:00 ላይ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር የውድድር ዓመቱን የመጨረሻ ጨዋታ ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ 4ለ0 በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፎ ዋንጫውን አንስቷል።
የፈረሰኞቹን የማሸነፊያ ግቦች ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ በ17ኛው ደቂቃ በጨዋታ እና በ54ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም አማኑኤል ገ/ሚካኤል በ89ኛው እና በ93ኛው ደቂቃ በጨዋታ አስቆጥረዋል።
ድሉን ተከትሎ ጊዮርጊስ በ65 ነጥብ የዋንጫው ባለቤት ሆኗል፡፡
በአጠቃላይ ለ28ኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮን በመሆን ተስተካካይ የሌለው ክለቡ፣ የዛሬው ዋንጫው ፕሪምየር ሊጉ በአዲስ መልክ ከተጀመረ ወዲህ ያሸነፈው 15ኛ ዋንጫው ነው።
ከዛሬው ጨዋታ በፊት በተካሔዱ ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ከጊዮርጊስ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ አጥብቦ ሊጉን ያደመቀው ፋሲል ከነማ፣ ዛሬ በተመሳሳይ ሰዓት በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡
3ለ2 በሆነ ውጤት ያሸነፈው ድሬዳዋ የነበረውን ብቸኛ ዕድል ተጠቅሞ በፕሪሚየር ሊጉ መቆየት ሲችል፣ በጊዮርጊስ የተሸነፈው አዲስ አበባ ከተማ፣ ሰበታ ከተማን እና ጅማ አባጅፋርን ተከትሎ ሦስተኛው ወራጅ ክለብ ሆኗል።
በዘንድሮው የሊጉ ውድድር 61 ነጥቦችን ሰብስቦ፣ በጊዮርጊስ በ4 ነጥብ በመበለጥ በሁለተኝነት ያጠናቀቀው ፋሲል ከነማ፣ በዛሬው ጨዋታ እስከ 77ኛው ደቂቃ በበረከት ደስታ እና በበዛብህ መለዮ ግቦች ሁለት ለባዶ ሲመራ ነበር የቆየው፡፡ ሆኖም ድሬዳዋ ከተማ ጋዲሳ መብራቴ በ77ኛው፣ ሄኖክ አየለ በ85ኛው እና አብዱራህማን ሙባረክ በ88ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ግቦች አሸንፎ ከመውረድ ተርፏል።
በአፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም በተካሔደ ሌላ ጨዋታ አዳማ ከተማ ሀዋሳ ከተማን 3ለ0 አሸንፏል፡፡ በዚህም ሀዋሳ የነሐስ ሜዳሊያ ለማሸነፍ የነበረውን ዕድል አጥቷል፡፡ በመሆኑም ሲዳማ ቡና ነገ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር የሚያደርገው የመጨረሻ ጨዋታ እየቀረው ሊጉን በሦስተኝነት ማጠናቀቁን አረጋግጧል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደ ዘንድሮው ለዋንጫ እጅግ አጓጊ የሆነ ትንቅንቅ የተካሔደባቸው የውድድር ዓመቶች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡