በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተመድ መርማሪዎች አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቃድ ማግኘታቸውን አስታወቁ


ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ
ፎቶ ፋይል፦ አዲስ አበባ

ኢትዮጵያ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት ውስጥ ፈፅማለች የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲያጣሩ የተሰየሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪዎች አዲስ አበባ እንዲገቡ ፈቃድ ማግኘታቸውን ዛሬ ኀሙስ አስታወቁ። ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም መግባት እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል።

የድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ተፈፅመዋል የተባሉ ጥሰቶችን የሚመረምር በየዓመቱ የሚታደስ ሥልጣን የተሰጠውና ሦስት የሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያዎች ያሉበትን አጣሪ ኮሚሽን ባለፈው ታኅሳስ መሰየሙ ይታወሳል።

"የኮሚሽኑ ምርመራ ትኩረት የሆኑት የሰብዓዊ መብቶች፣ የሰብዓዊነትና የስደተኛ ህግጋት ጥሰቶች እና በደሎች አሁንም በግጭቱ ውስጥ እየተሳተፉ ባሉ የተለያዩ ወገኖች ያለምንም ተጠያቂነት መቀጠላቸው እንደሚያሳስባቸው የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር አመልክተዋል።

አክለውም የኢትዮጵያ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ የሚፈፀሙ ጥሰቶችን የማስቆምና ተጠያቂዎችን ለፍርድ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበት ኮሚሽኑ አበርትቶ እንደሚያሳስብ መግለፃቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

“ኦሮምያ ክልል ውስጥ የተፈፀሙትን ጨምሮ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሱ የጭካኔ አድራጎቶች በጥልቅ አሳስበውናል” ሲሉ ሊቀመንበሯ አክለው ተናግረዋል።

“ሲቪሎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚያቀጣጥል የጥላቻ ንግግርና በጎሣ ማንነትና በፆታ ላይ የተመሠረቱ ጥቃቶች እንዲፈፀሙ ቅስቅሳ ማካሄድ የጭካኔ ወንጀል አድራጎቶችን እንደሚያስከትሉ እንደቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚወሰድ ነው” ብለዋል

በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን በግጭቱ ውስጥ በሚሣተፉት በሁሉም ወገኖች ተፈፅመዋል የተባሉትን ጥሰቶች የሚመረምር ሲሆን የሽግግር ፍትኅና የብሄራዊ ዕርቅ መመሪያም በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።

ከኢትዮጵያ የፍትኅ ሚኒስትር ጋር ባለፈው ግንቦት የተገናኙት የመንግሥታቱ ድርጅት መርማሪዎች ግጭት በተካሄደባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች የመብቶች ጥሰቶች ሰለባዎች ናቸው የተባሉ ሰዎችን ለማነጋገር ፈቃድ የጠየቁ ሲሆን አዲስ አበባን ለመጎብኘት ከኢትዮጵያ መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን የኮምሽኑ ሊቀ መንበር አስታውቀዋል።

ሊቀመንበሯ በማከልም “አዲስ አበባ ላይ በምናደርገው ውይይት መርማሪዎቻችን ጥሰቶች ወደተፈፀሙባቸው አካባቢዎች መግባትና ከተጎጂዎችና ከዕማኞች ጋር ለመነጋገር እንዲችሉ ፈቃድ ያገኛሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

XS
SM
MD
LG