በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፅንስን ማቋረጥ በአሜሪካ፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱና ምላሾች


በይናይትድ ስቴትስ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ደጃፍ የነበሩ ጽንስ ማቋረጥ የሚከለክለውን ሕግ የተቃወሙ ሰልፎች
በይናይትድ ስቴትስ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ደጃፍ የነበሩ ጽንስ ማቋረጥ የሚከለክለውን ሕግ የተቃወሙ ሰልፎች

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሴቶች ፅንስን ማቋረጥ እንዲችሉ ላለፈው ግማሽ ምዕት ዓመት ህገ መንግሥታዊ ከለላ ሰጥቶ የቆየው ‘የሮ እና የዌድ ሙግት ጉዳይ” እየተባለ የሚጠራውን ህግ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ከትናንት በስተያ ዓርብ ውድቅ ካደረገ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ አሜሪካዊያን ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥ በፍርድ ቤቱ ፊት ለፊትና በሌሎችም ከተሞች የድጋፍና የተቃውሞ ይዘት ያላቸውን ሰልፎች እያደረጉ ነው።

በወግ አጥባቂ ዳኞች የበላይነት የተያዘው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያለፈውን ህግ የገለበጠው 6 ለ 3 በሆነ አብላጫ ሲሆን ውሳኔው ግማሽ በሚሆኑ ስቴቶች ውስጥ ፅንስ ማቋረጥ ሙሉ በሙሉ እንዲታደግ ሊያደርግ እንደሚችል ሮይተርስ ትናንት ዘግቧል።

ወግ አጥባቂው ዳኛ ክለረንስ ታመስ ለውሣኔያቸው ማስረገጫ በፃፉት አስተያየታቸው የአሁኑ ውሣኔ ሌሎችም ቀደም ሲል ተላልፈው የነበሩ “የፅንስ ማስወገጃ ወይም መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን የመጠቀም መብቶችን፣ ለተመሣሣይ ፆታ ጋብቻ በሃገር አቀፍ ደረጃ የህግ ዕውቅና መስጠትን” የመሳሰሉ ድንጋጌዎችን መልሶ ወደ መፈተሽ ሊወስድ እንደሚችል አመላክተዋል።

ትናንት ከሰዓት በኋላ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ደጃፍ የነበሩት ሰልፎች ስፋት ወደ ማምሻው እየገዘፉ የሄዱ ሲሆን በተለይ ከፍ ባለ አጥር በተከለለው የህንፃው ፊት ለፊት የተሰበሰበው ሰው ውሣኔውን አጥብቶ የሚቃወምና ፅንስን ለማቋረጥ መብት መከበር የሚሟገት እንደነበረ የሮይተርስ ዘገባ አክሎ ጠቁሟል።

“ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይጨንገፍ!”፤ “ሴቶችን ሳይሆን የጦር መሣሪያን ተቆጣጠሩ!” የሚሉ መፈክሮች አደባባይ የዋሉ ሲሆን ውሳኔውን ደግፈው የወጡት ሰልፈኞችም “ማህፀን ውስጥ ያለ ህይወትም ሊከበር ይገባል”፤ “እንዲጨነግፍ የተደረገ ህፃን ምርጫ አልተሰጠውም” የሚሉ አስተያየቶችን አሰምተዋል።

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደተላለፈ በብርቱ ቃላት ያወገዙ ሲሆን ትናንት በሰጡት አስተያየት ግዛቶቹ ፅንስ የማቋረጥ እገዳውን እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉት በቅርብ እንደሚከታተሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የቫቲካን ባለሥልጣኗ አንድሬዓ ቶርኒየሊ በፃፉት ርዕሰ አንቀፅ “ፅንስ ማቋረጥን የሚቃወሙ ተሟጋቾች ይልቅ በሌሎች የህይወት ጠንቅ በሆኑ የጦር መሣሪያ በቀላሉ ማግኘትን፣ ድህነትን እያሻቀበ የመጣውን የእናቶች ሞት በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩሩ ይገባቸዋል” ብለዋል።

ባለፈው ወር የወጣ በሮይተርስና ኢፕሶስ የተካሄደ የህዝብ አስተያየት ቅኝት ውጤት አብዛኞቹን ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካን ጨምሮ 71 ከመቶ አሜሪካዊያን ፅንስን የማቋረጥ ውሣኔ ጉዳይ ለሴቶችና ለሃኪሞቻቸው ሊተው እንደሚገባ እንደሚያምኑ ሮይተርስ በዘገባው ጠቁሟል።

የከትናንት በስተያው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሣኔና ጫናው የፊታችን ጥቅምት 29/2014 ዓ.ም. በሚካሄደው የአማካይ ፕሬዚዳንታዊ ዘመን ምርጫ ላይ ለሁለቱም ፓርቲዎች ብርቱ ፈተና እንደሚጋርጥ ተንታኞች እየተናገሩ ነው።

XS
SM
MD
LG