በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ የምግብ እጥረት መባባሱንና የእርዳታ አቅርቦት መሟጠጡን ተ.መ.ድ አስታወቀ


በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ግጭት እና በደቡብ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ድርቅ ምክንያት ከ20 ሚሊየን በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የደረሰው የረሃብ አደጋ እየጠነከረ መሄዱን ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አፋጣኝ እርዳታ ካልተገኘ ለእርዳታ የተዘጋጀው ምግብ በሚቀጥለው ወር ሊያልቅ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

የተባበሩት መንግስታት የዓለም ምግብ ተቋም ትላንት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ለ19 ወራት የተካሄደው ግጭት በአፋር፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የሚኖሩ 13 ሚሊየን ሰዎችን ሰብዓዊ ርዳታ ጠባቂ አድርጓቸዋል። በደቡብ እና በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ ደግሞ ለአራት ተከታታይ ወቅቶች ዝናብ ባለመዝነቡ ወደ 7.4 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች በየእለቱ ከረሃብ ጋር ቀናቸውን ይጀምራሉ።

ግጭቱ እና ድርቁ ተዳምሮ የዋጋ ግሽበት እንዲባባስ ማድረጉንም የገለፀው የዓለም ምግብ ድርጅት፣ የምግብ ዋጋ ባለፈው አመት ሚያዚያ ወር ከነበረበት በ43 ከመቶ የጨመረ ሲሆን በተለይ የምግብ ዘይት ዋጋ 89 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

"በተለይ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በኢትዮጵያ የምግብ እጥረትን ሊያብብሰው ይችላል" ያለው የድርጅቱ ሪፖርት፣ የምግብ ተቋሙም ሆነ መንግስት ሶስት አራተኛ ስንዴ የሚያገኙት የነበረው ከዩክሬን እና ከራሽያ በመሆኑ የስንዴ እና የማዳበሪያ ዋጋ ገበሬዎች ከሚችሉት አቅም በላይ ሊሆን እንደሚችል፣ ይሄ ደግሞ የዚህ አመት ምርትን አደጋ ላይ እንደሚጥለው አስጠንቅቋል።

እስካሁን በትግራይ ክልል 800 ሺህ ሰዎች፣ እንዲሁም በአፋር እና አማራ ክልሎች 163 ሚሊየን ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ርዳታ እንደተደረገላቸው የገለፀው የመንግስታቱ ድርጅት ተቋም፣ በሀገሪቱ ለሚገኙ 700 ሺህ ስደተኞች ይሰጥ የነበረውን የምግብ ርዳታ ግን በገንዘብ እጥረት ምክንያት ከግማሽ በላይ ማቋረጡን አስታውቋል።

ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት በሀገሪቱ ሊመግባቸው የሚገባ 11 ሚሊየን ሰዎችን ለመድረስም 470 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ርዳታ እንደሚያስፈልገው ግለፆ ለእርዳታ ሰጪዎች ጥሪ አቅርቧል።

XS
SM
MD
LG