በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጌታቸው ረዳ በሰላም፣ በእርዳታና በኤርትራ ጉዳይ


የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ

በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና ትግራይን እያስተዳደሩ ባሉት ባለሥልጣናት መካከል የሰላም ድርድር እንዲጀመር እየጣሩ ያሉ “ሦስተኛ ወገን” ያሏቸው ልዑካን ወደ መቀሌ እየተመላለሱ መሆናቸውን የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የክልላቸው ባለሥልጣናትም ለሰላም ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ጌታቸው ማስታወቃቸውን ሪፖርተራችን ሙሉጌታ አፅብሃ ከመቀሌ ዘግቧል።

የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከሰባት ጊዜ በላይ መመላለሳቸውንና ትናንትም የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች መቀሌ እንደነበሩ ቃል አቀባዩ አመልክተው ክልሉ ውስጥ አለ ያሉትን ሰብዓዊ ቀውስ ልዑካኑ እንዲያውቁ መደረጉን፣ አይደር ሆስፒታልንም መጎብኘታቸውንም ገልፀዋል።

በነዳጅና በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ህዝቡ እየተሰቃየ መሆኑን ልዑካኑ በአካል ተገኝተው ማየታቸውንና መጠለያ ውስጥ ስላሉና ችግር ውስጥ ስለሚገኙ የምዕራብ ትግራይ ተፈናቃዮችም ማብራሪያ እንደተሰጣቸው አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

የእርዳታ አቅርቦትን በሚመለከት ያላቸው አቋም ጠንካራ መሆኑን አውሮፓዊያኑ ልዑካን እንደገልፁላቸው አቶ ጌታቸው አመልክተዋል።

የልዑካኑ አባላት ክልሉን እያስተዳደሩ ካሉት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካዔልና ከሃይማኖት መሪዎች ጋርም ተገናኝተው መነጋገራቸውን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

ምንም እንኳ ወደ ክልሉ የሚገባው እርዳታ መጠን እየጨመረ ቢሆንም በነዳጅ እጥረት ምክንያት ወደ 30 ሺህ ሜትሪክ ቶንስ እህል ለህዝቡ ማድረስ እንደተሳናቸውና እርዳታው መጋዘን ውስጥ እንደተከማቸ መሆኑን አመልክተዋል።

“የትግራይን ህዝብ ህልውናና ደኅንነት ለሚያረጋግጥ የሰላም አማራጭ ቅድሚያ እንሰጣለን” ያሉት አቶ ጌታቸው “ካልሆነ ግን - ምንነቱ በዘገባው ውስጥ ወዳልተጠቀሰ “ሌላ አማራጭ” ወዳሉት እንደሚሄዱ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው አክለውም “የዐቢይ መንግሥት” እያሉ የጠሩት ፌዴራሉ መንግሥት “እውነት ይሁን አይሁን ባናውቅም፤ የሰላም ፍላጎት እንዳለው በፓርላማ ጭምር አሳውቋል” ብለው የኤርትራን መንግሥት “የሰላም ዕድልን በማደናቀፍ” ከስሰዋል።

ለዛሬው የአቶ ጌታቸው ክሥ ከኤርትራ ባለሥልጣናት በቀጥታ የተሰማ ነገር ለጊዜው በእጃችን ባይኖርም በየጊዜው በሚሰጧቸው መግለጫዎች ግን የህወሓትን መሪዎች በ"ፀረ-ሰላም” ኃይልነትና በ“ሽብርተኛነት” ይወነጅላሉ።

አቶ ጌታቸው ረዳ በዛሬው መግለጫቸው የኤርትራ ኃይሎች እስካሁን የያዟቸው የትግራይ አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁመው “በሰላም ካልወጡ በኃይል እንዲወጡ ይደረጋል” ብለዋል። በኤርትራ ተይዘዋል ያሏቸው አካባቢዎች የትኞቹ እንደሆኑ ግን አልገለፁም።

XS
SM
MD
LG