አሜሪካዊያን በ’ያመቱ በወርሐ ሰኔ ሶስተኛ እሁድ የሚዘከረው የአባቶች ቀንን እያከበሩ ይገኛሉ። ይሄ ቀን የቤተሰብ አባላት ለአባቶች ያላቸውን ክብር የሚገልጹበት ፣ አባቶችን በስጦታ የሚያንቆጠቁጡበት ፣ ሬስቶራንቶች አባቶችን ለግብዣ ይዘው በወጡ ቤተሰቦች የሚጨናነቁበት ነው ።
ሂስቶሪ ዳት ካም History.com የተሰኘው ታሪክ መዝጋቢ አውታር የመጀመሪያው የአባቶች ቀን የተከበረው በጎረጎሳዊያኑ ሐምሌ 5/1908 እንደሆነ ይጠቁማል። በወቅቱ በምዕራብ ቨርጂኒያ የሚገኝ ቤተ-ክርስቲያን በሞሞንጋ በሚባል ስፍራ ፌርሞንት የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ላይ በደረሰ ፍንደታ ህይወታቸውን ላጡ 362 ወንዶች መታሰቢያ ስነ-ስርዓት አዘጋጀ ። ስነስርዓቱ አንዴ እንዲደረግ እንጅ በ’ያመቱ እንዲከናወን የታቀደ አልነበረም ።
አውታሩ እንደሚያወሳው ፣ በቀጣዩ ዓመት ሶኖራ ስማርት ዶድ የተባሉ ከ5 የቤተሰብ አባላቶቻቸው ጋር ሚስታቸውን ባጡ አባት ያደጉ ሴት የስፖኬን-ዋሺንግተን ነዋሪ፣ በ’ያመቱ የአባቶች ቀን እንዲከበር ማህበረሰቡን ማግባባት ጀመሩ ። ተሳካላቸው ። በ1910 የዋሺንግተን ግዛት የመጀመሪያውን ግዛት አቀፍ የአባቶች ቀን አከበረ።
ይሄ ስነ-ስርዓት ቀስ በቀስ በመላ አሜሪካ ተስፋፋ ። አውታሩ በያመቱ አሜሪካዊያን በዚህ ቀን ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ለአባቶች ለሚሰጥ ስጦታ እንደሚያወጡ አስታውቋል ።