የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ተሳታፊ አካላት ግጭቱን ለማርገብና ሰላማዊ መፍትሄዋችን ለማፈላለግ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አደረቁ።
ሊቀመንበሩ የህብረቱን የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ፣ የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት፣ “የብሄራዊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት፣ የጦር ምርኮኞች እንዲለቀቁ መደረጉ፣ ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ፣ ለሰብአዊነት ሲባል ተኩስ እንዲቆም መደረጉ እና የትግራይ ኃይሎች ከተቆጣጠሯቸው የአፋር አካባቢዎች መውጣታቸው” መተማመን ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉልህ እርምጃዎች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
ሊቀመንበሩ አክለው ለሰብአዊነት ሲባል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉን ተከትሎ ለተጎዱ ክልሎች የሰብአዊ አቅርቦትና ድጋፍ በማቅረብ ረገድ የታዩ መሻሻሎችን የአፍሪካ ህብረት በጸጋ እንደሚቀበላቸው ተናግረዋል፡፡
የተገኙት ውጤቶች የመጡት የህብረቱ ተወካይ የሆኑት ኦባአሳንጆ በሁለቱ ወገኖች መሀከል በመላለስ ባደረጉት ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ነው ያሉት ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጠበኝነትን የማቅዝቀዝ እና ግጭቶችን የማርገብ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።
ሊቀመንበሩ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሃት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የወሰዷቸውን ርምጃዎች አድንቀው በፖለቲካዊ ውይይት ችግሮችን ለመፍታት የጀመሩትን መንገድ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያበረታቱ ሲሆን፣ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት እንዲደግፉ ጥሩ አቀርበዋል።